http://twondifraw.blogspot.com/

Monday, June 1, 2020

ያልተዘመረለት



በአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ዉስጥ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴትን በተግባር ከትህትና ጋር የሚያሳይ ትጋቱ ከንብ ጋር የሚስተካከል አንድ ወሳኝ የሆነ አካል አለ፡፡ ይህ አካል በስራ ትጋት ብቻ ሳይሆን በስነ-ግጥም በአካባቢያዊ አባባሎች፣ በሽለላ እና ቀረርቶ በአጠቃላይ በስነ-ቃል ችሎታዉ ጎልቶ ይታወቃል፡፡ ቀን ሲሰራዉ የዋለዉን፣ ወደ ፊት ሊሰራ ያሰበዉን፣ ሀላፊዉንና መጻኢዉን ኩነቶች እያነሳ ዱሩን፣ ሸንተረሩን፣ ጉሙን፣ ጎርፉን፣ አእዋፉን፣ ሰብሉን፣ አበባዉንና እሸቱን በዜማ እየነካካ በፉጨት እያማለለ በዋሽንት እያታለለ የሀገሬዉን ሰዎች ያዝናናል የቀዘቀዘዉን መንደር ያሞቃል፡፡ ይህ አካል ታድያ በግብር ስሙ እረኛ ይባላል፡፡ እረኛዉ በቀየዉ ሲኖር ከሚታወቅባቸዉ አበይት ስራዎቹ መካከል አቃቢነት ነዉ፡፡ አቃቢ ማለት ጠባቂ ሲሆን እረኛዉ ከሁሉም ነገር ሰብልን እና ከብቶችን በመጠበቅ ግብሩ ይታወቃል፡፡ ሰብሉን ሲጠብቅ ታድያ ተግቶና ታጥቆ ነዉና አስቀድሞ ለወፉ ወንጭፍ ለከብቱ ጅራፍ ፈትሎ ያዘጋጃል፡፡ ቀጥሎ ከሰብሉ መሬት መሃል ወይም ዳር ላይ ማማ ይሰራል፡፡ ከሰራዉ ማማ ራስ ላይ በኩራት ቆሞ እየተጎማለለ የሰበሰበዉን ጠጠር በወንጭፍ አሽከርክሮ በመወርወር በበልግ የዘራዉን ማሽላዉን፣ ገብሱን፣ በቆሎዉንና ስንዴዉን በመኸር ወቅት ከማማዉ ላይ ቆሞ በአራቱም ማእዘን እየተዘዋወረ ተግቶ ይጠብቃል፡፡ ከዝንጀሮዉ፣ ከፍልፈሉና ከአእዋፋቱ ጋር ሲፋለም ሌሊት ወጥቶ ሌሊት ይገባል፡፡ ይህ አቃቢነቱ ሰብሉ እስኪጎመራ ብሎም እስኪደርቅ ድረስ ይዘልቃል፡፡
ሌላኛዉ የእረኛዉ አቃቢነት ደግሞ ከብቶቹን መጠበቅ ነዉ፡፡ ቆየት ባሉት ዘመናት እረኛ ከብቶቹን የሚያረባዉ ደጋማዉን ቀየዉን ለቅቆ በመሄድ በርሀ ወርዶ  ጎጆ በመቀለስ ነበር፡፡ ይህ ዘዴ በአካባቢዉ ህብረተሰብ ዘንድ ደረባ በመባል ይታወቃል፡፡ በደረባ ጊዜ እረኛዉ የሚያርሱ በሬዎችን ከደጋዉ ትቶ ላሞችን እና ጊደሮችን ከነጥጆቻቸዉ ይዞ ለሰዉ ልጅ ሳይቀር የሚያጓጓዉን ረጃጅም እና ወዛም ሳር ለመመገብ በርሀ ወርዶ ይከትማል፡፡ ከዚያም በጨፈቃ የተገደገደች ጊዚያዊ ጎጆ ከበርሃዉ እሾሀማ እንጨቶች ለቅሞ ይቀልሳል፡፡ የበርሃው ተናካሽ ፍጡራን ስለሚያስቸግሩት ለመኝታዉ ከመሬት ከፍ አድርጎ በባላ ላይ ጠንካራ እንጨቶችን ሰካክቶ ቆጥ ይሰራል፡፡ ጊዜያዊ መኖርያዉን ከበርሃ ያደረገው እረኛ ከወር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ወደ ደጋዉ ብቅ እያለ ዘመድ ይጠይቅና የእለት ስንቅ አስበስሎ በአገልግሉ አንግቶ ዉኃ በቅል ይዞ ሲያሻዉ በፉጨት ሲፈልግ በድምጽ አባት አደር በሆኑ ዜማዎች ቅራርቶዉንም ዘፈኑንም ልብን በሚሰርቅ ሁናቴ እያንጎራጎረ ይመለሳል፡፡ ወደ ደጋዉ ሲወጣ ለዘመደቹ ለእርሻ እና ሌሎች ስራ የሚዉል የበርሃዉን ሲሳይ ለጎጆ ቤት ክዳን የሚሆን ፊላ የተባለዉን ሳር፣ ለሽማግሌዎች ምርኩዝ የሚሆን ትለም ከተባለ ዛፍ የተዘጋጀ ሽመል፣ የምሳር እጀታ፣ የጅራፍ ልጥ፣ ቀበርቾ፣ ድግር እና ሌሎች ማለፍያ ሲሳይ ተሸክሞ ከደጋዉ ይዘልቃል፡፡ እረኛዉ በበርሀ ህይወቱ ማታ እሳቱን እያነደደ ዋሽንቱን እየነፋ ሌሊቱን ያዋግድና ከቆጡ ገብቶ ጋደም ይላል፡፡ የሌሊት አዉሬዎች በተለይ ነብርና ጅብ ከብቶቹን እንዳይተናኮሉበት ከመኝታዉ በዉድቅቱ ሌሊት ደጋግሞ እየተነሳ ይሰልላል፡፡
እረኛዉ ከቤቱ በራቀ ወቅት ስንቁን የሚያገኘዉ ደጋ ሲሆን ከሰብሉ ገብቶ እሸቱን በርሀ ሲዉል ደግሞ ከበረት ገብቶ ወተቱን በማማረጥ እና በመሸምጠጥ ነዉ፡፡ እሸቱን በሁለት መንገድ ይመገባል፡፡ የመጀመርያዉ ጥሬዉን ምንም ማብሰል ሳያስፈልገዉ ስንዴና ገብስ ከሆነ የእሸቱን ምርቅ በጥፍሮቹ ነቅሎ አስወግዶ በመዳፎቹ እያሸ ባቄላና አተር ከሆነም ቦጥቡጦ በኪሱ ከቶ አልያም በፎጣው ታቅፎ እየፈለፈለ ይቅማል፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ሁሉን የእሸት አይነት በእሳት በማብሰል በቆሎ ከሆነ ጠብሶ ስንዴ ከሆነ ደግሞ አንኩቶ ነዉ፡፡ ድርቅ በሆነ ዘመን እረኛዉ ታላቅ ስደት ከደጋዉም ከበርሀዉም ይገጥመዋል፡፡ እንደ ደጉ ዘመን ለምለም እሸትና ትኩስ ወተት ማግኘት የዉሀ ሽታ ይሆንበታል፡፡ በእንዲህ አይነት ክፉ ዘመን የነበረን እረኛ ገጠመኝ አልያም ታሪክ እንደሚከተለዉ ተደርሶለታል፡፡

አልቦ ወተት
አልቦ ወተት ከላሚቷ፣
እረኛዋ ሊጠጣ ሲያመነታ፣
ሙጃ አብልቶ ጨዉ አልሶ፣
እጅ ነስቶ ተጎንብሶ፣
የአጋተ ጡትዋ ቢያስመኘዉ፣
እረኛዉ ወተት ወተት አሰኘዉ፡፡
ቅሉን ለግቶ እግሩዋን ግዶ፣
እምቦሳዋን ግጭ ገብቶ ከጥባት አስጥሎ አናዶ፣
ከግርዋ መሃል ተቆጥጦ፣
አይኑን ጋትዋ ጫፍ ላይ አፍጥጦ፣
በጣቶቹ አድፈጥፍጦ፣
አፍረጥርጦ ንጦ፣
ግጩን ለቆ ግድዋን ፈትቶ፣
ከደረባዉ ጎጆዉ ገብቶ፣
ከቆጧ ላይ ዘሎ ወጥቶ፣
ጉምጁ እረኛ ሊጠጣ፣
ቅሉን ይዞ አንጋጠጣ፡፡
አይ ክፉ እድል የድርቅ እጣ፣
ከደረቱ ቢሰበቅ ምላሱን ቢስብ ቢያወጣ፣
ከጉሮሮዉ የምትመጣ፣
ጠብታ እንኳን ከቅሉ አጣ፡፡
በቅል ወተት አልቦ ነበርና፣
ምን ፉት ይበል እረኛዉ አንገቱንስ ቢያቀና፡፡

ይህ ሲሳይ የራቀዉ እራብ የገረፈዉ ትጉሁ የበርሃ እረኛ በእንዲህ አይነት ጊዜ ወደሌላኛ ማግመጫዉ ወደ እሸቱ ሄዶ አምሮቱን ሊወጣ ይገደዳል፡፡ ድንቹ ከደረሰ አንካሴዉን ለበቆሎዉ እና ማሽላዉ ደግሞ ማጭዱን፤ ለአተሩና ባቄላዉ ስልቻዉን  ይዞ ከደጋዉ ይዘልቃል፡፡ ከዛም ልቡ ከፈቀደው ሆዱ ከወደደዉ ማሳ ገብቶ ፍላጎቱን አርክቶ እየፏለለ ይመለሳል፡፡
በደጋዉ አለም ከድርቅ መቅሰፍት ተርፎ ለአካለ መጠን የደረሰ አዝመራን በማዳሸት፣ በመጋጥና በማበላሸት የእረኛዉን ልፋትና ተስፋ ከአፈር ደባልቃ ከንቱ የምታደርግ እሱ ራቡን ሊገድል በሄደ ወቅት ሰብሉን ቀድማ ገድላ የምትገኝ አንድ ወፈፌ አዉሬ አለች፡፡ እርስዋም ጃርት ትባላለች፡፡ ጃርት በአንድ አካባቢ የሚገኝን የተለያዩ ገበሬዎች ሰብል ድንበር ሳያግዳት እገሌ የጌታ ዘር ነዉ ይገለኛል እገሌ ደግሞ ጭሰኛ ነዉ ምን ያመጣል ሳትል ደስ ካላት ገብታ በልታ ደስ ካላላት ደግሞ አልፋ ሌላዉ ጋ በመሄድ በአንድ ሌሊት ብዙ አዝመራ አበላሽታ ታድራለች፡፡ ይህንን አስቀድሞ የሚያውቅ እረኛ በመኸር ወቅት በጠዋት ገስግሶ ተነስቶ ወደ ማሳዉ ይሄድና የተበላ ሰብል ካለ አዝኖ ካልተበላም ተደስቶ እሸቱን እየቃመ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፡፡ ታድያ የስነ-ቃል ባለጸጋ ነዉና ይህን ማዘኑንና መደሰቱን ለህብረተሰቡ የሚገልጸዉ በስነ-ቃል ነው፡፡ ስነ-ቃሉ እንደየ ጉዳቱ መጠን፣ እንደየ ድርጊቱ ሁኔታ ይወሰናል፡፡
በጥያቄና መልስ መንገድ የሚቀርብ ስነ-ቃል ሲኖር  በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ባሉ ጃርቶች መካከል የተደረገ ሌሊት የሰሩትን ጀብዱ የሚያሳይ ቃለ ምልልስ ነዉ፡፡ ይህ እረኛ ሰብሉ  የተበላበትን ወይም ሰብሉ ምንም ያልተነካበትን ገበሬ ስም እየጠቀሰ ጃርቶች ያን ሰብል ለምን እንደበሉት ወይም ደግሞ ለምን እንዳለፉት እርስ በራሳቸዉ ሲነጋገሩ እንደሰማ ሆኖ  በራሱ ጊዜ የደረሰውን እንደሚከተለዉ በጥኡም ዜማ ይተርካል፡፡
ለምሳ ጃርቶች ጌትነት የተባለ ገበሬን የበቆሎ አዝመራ በጣም በጎዱት ጊዜ
ጃርት 1 ፡ ይሄ የማነዉ በቆሎ? ስትል ትጠይቃለች
ጃርት 2 ፡ የአያ ጌትነት፡፡  በማለት ትመልስላታለች
ጃርት 1 ፡ የዛ የመልካሙ?
ጃርት 2 ፡ አዎ፡፡
ጃርት 1 ፡ ያዥዉ በመሙ[1]፡፡
ጃርቶች ሀብታሙ የተባለን አርሶ አደር ድንች ሳይበሉ አልፈዉ የሌሎችን ገበሬዎች ድንች በበሉ ጊዜ ደግሞ
ጃርት 1 ፡ ይሄ የማን ነዉ ድንች?
ጃርት 2 ፡ የአያ ሀብታሙ
ጃርት 1 ፡ የዛ የተላፋፊዉ?
ጃርት 2 ፡ አዎ
ጃርት 1 ፡ ተይዉ እለፊዉ
ጃርቶች የጌትነትን በቆሎ ለምን በጣም እንደጎዱትና የሀብታዉን ድንች ለምን እንዳለፉት እረኛው ተመራምሮ የደረሰበትን በዚህ መንገድ ለህብረተሰቡ ይገልጣል፡፡
እረኛው ከጥያቄና መልስ በተጨማሪ የጃርቶቹን ጥፋት በግጥም መልኩ ያቀርባል፡፡
አንድ ሙሉጌታ ከተባለ ገበሬ የበቆሎ ሰብል ገብታ በቆሎዉን ግጣ ጨርሳና አገዳዉን ከመሬት ጨፍጭፋ ጥላ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰች ጃርት እረኛዉ ሲነጋጋ ሄዶ የተበላዉን ሰብል ያይና ጃርቷ ለሰብሉ ባለቤት ማለትም ለአቶ ሙሉጌታ ምን እንዳለች በስነ-ቃል እንዲህ ብሎ ባለቤቱን ያረደዋል፡፡
ሙሉጌታ አባተ ወላንሳ ወላንሳ፣
ፍሬዉን በላዉት ገለባዉን አንሳ፡፡
ከአያ አላምር ፈለቀ ማሳ ገብታ ካለምንም ስጋት ሌሊቱን ሙሉ ድንቹን ስትግጥ አድራ ከመጠን በላይ ከመጥገቧ የተነሳ ወደ ጉድጓዷ መሄድ ተቸግራ በዛው በድንቹ መሃል ስትንጎራደድ ለተገኘችዋ ጃርት ደግሞ
አላምር ፈለቀ ቶፋ ግዛልኝ፣
ጥራጥሬው ድንች ሆዴን ጎጠረኝ፡፡
አንድ አጤ ፈንታ የምትባል ባልዋ ሞቶባት ብቻዋን የምትኖር የገበሬ ሚስት ነበረች፡፡ ሁሉንም መሬቶቿን የእኩል ሰጥታ በገበሬ እያሳረሰች ጓሮዋን ደግሞ ራሷ ታስጎልማለች፡፡ ጓሮዋን በቆሎ ታዘራና በዉስጡ ደግሞ ክረምት እህል በሚያጥርበት ሰዓት ቶሎ እንዲደርስላት ድንች፣ ቃሪያና ዱባ ራሷ ትተክላለች፡፡ ነገር ግን ያች ክፉ ጃርት ድንቹ ገና ማበብ ሲጀምር ዱባው ሲያኮረኩር በውድቅቱ ሌሊት ትገባና በቅጥ ያልደረሰውን ድንችና ዱባ ስሩን ነቅላ ግጣና ገምጣ እንዳልሆነ አድርጋ ትሄዳለች፡፡ ወ/ሮ አጤ በጠዋት ተነስታ ስትሄድ ለክፉ ቀን ይደርሱልኛል ብላ የተከለቻቸው ሰብሎች ያለ እድሜያቸው ተቀጥፈዉ ታገኛቸዋለች፡፡ ከዚያም ንዴቷና ቁጭቷ መድረሻ ሲያሳጧት እጆቿን ከፍ አድርጋ እያጨበጨበች እየየ ስትል ታረፍዳለች፡፡ ይህ ድርጊቷ በእየለቱ የተለመደ ሆነ፡፡ ይህንን ያየ እረኛ እንደሚከተለው ተቀኘላት፡፡
እመት አጤ ፈንታ ምኗን ትድራለች፣
በነጋ በነጋ ታጨበጭባለች፡፡
አንድ አንዳርጌ አሳዬ የተባለ ባለጉዛም ገበሬ ነበር፡፡ ለቁጥር የሚያታክቱ የቀንድና የጋማ ከብቶች፣ ጉረኖ የማይችላቸው በጎችና ፍየሎች ነበሩት፡፡ ፍየሎች በጣም አስቸጋሪዎች የነበሩ ሲሆኑ ወደ መሰማሪያ ሜዳ ሲሄዱ የሰው ሰብል ውስጥ ዘለው በመግባት ሜዳ ውለው ከቤት ሲመለሱ ደግሞ ከጥራጥሬው እህል ማለትም ከባቄላው፣ ሽምብራውና በቆሎው ጎተራ ላይ ተንደርድረው እየተሰቀሉ በመብላትና በማፍሰስ ጠባቂ እረኞቻቸውን በጣም ያሰቃዩ ነበር፡፡ አንዳርጌ የበቆሎ ሰብሉን በእጅጉ የጎዳችበትን ጃርት ለመግደል ንጋቱ ከተባለ ሲሶ ተካፋይ እረኛው ጋር አንድ ቀን አንድ ዘዴ ይዘይዳል፡፡ ጃርቷ ሲቀርቧት በእሾኋ ስለምትወጋ ያም ሆኖ ከጀርባዋ የፈለገ ቢመቷት ስለማትሞት ንጋቱ ጃርቷን በረጅም ዘንግ ከጀርባዋ ሆኖ እየነዳ ወደ ጉድጓዷ ስትሄድ አንዳርጌ ደግሞ ከጉድጓዷ አጠገብ ሆኖ አፍነጫዋን መትቶ ለመግደል ተስማሙ፡፡ እንዲህ እያደረጉ ብዙ ጊዜ ቢደክሙም ተሳክቶላቸው ጥቂት ጃርቶችን ሲገድሉ ብዙዎችን ግን ሊገድሏቸው አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ የቀየው እረኛ የጃርቷን ስሞታ በሚከተለው መንገድ አሰማላት፡፡
እድሌ ነው እንጅ ኮከቤ ቢሰበር፣
ካንዳርጌ ፍየሎች መች እከፋ ነበር፡፡
ንጋቱ መልካም ሰው ሲቸበችበኝ፣
አንዳርጌ ክፉ ሰው ሙጩን ጠረገኝ፡፡
ታድያ በጃርቶች መካከል የተደረገዉን የመጀመርያዉንም ቃለ ምልልስ ሁለተኛዉንም ግጥም የሚናገርበት እረኛዉ የራሱ የሆነ የሚስብና አእምሮ ዉስጥ ተቀርጾ የሚቀር የራሱ የሆነ ዉብ ዜማ አለዉ፡፡ ችግሩ ዜማውን በድምጽ ማሰማት ብቻ እንጅ በጽሁፍ ማስነበብ ስላልቻልኩ (ለቅዱስ ያሬድ በድፋት፣ ርክርክ፣ ቅናት፣ ሰረዝ …. ምልክቶች የተቻለ ለእኔ ግን አልተቻለኝም) ሙሉዉን የእረኛዉን ችሎታ እዚህ ላይ ማቅረብ አልተቻለኝም፡፡ ዜማዉን ነጥየ ስነ-ግጥሙንና ስነ-ቃሉን ብቻ ለማቅረብ ተገድጃለሁ፡፡ የዜማዉን ይዘት ምን እንደሚመስል ትንሽ ምናባዊ ምስል ለመስጠት ያህል ለማስረዳት ብሞክር ግን እንዲህ ይመስለኛል፡፡ ይህ የጃርቶችን ቃለ-ምልልስ እረኛዉ የሚያዜመዉ ቀዝቀዝ ባለ ድምጽ ሆኖ ዝግ ባለ የቃላት ፍሰት ለስለስ ባለ ዜማ በማንቆርቆር ነዉ፡፡ ከኢትዮጵያ የቅኝት ስልቶች ከየትኛዉ ሊመደብ ይችላል ብትሉኝ ከትዝታ ማይነር ቅኝት ጋር ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡በስተመጨረሻም እኔ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ያልተዘመረለት በሚል የሬድዮ መርሀ ግብር ታሪካቸዉ ሲወሳላቸዉና ሲዘመርላቸዉ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ እረኛ አዚሞ ዜማዉ ያልተሰማለት እና ተናግሮ ንግግሮቹ ያልተነገረለት ነዉና ያልተዘመረለትና ያልተነገረለት ተብሎ እረኛዉ ቢዘከር እንዴት በተገባዉ ነበር እያልሁ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ስለእረኛዉ ትዘምሩለት ዘንድ በእጩነት አቅርቤላችኋለሁ፡፡

23/06/2008 ዓ.ም ደ/ወርቅ




[1]እመም ማለት በአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ ሰብሉን ለማረም ወይም ለማጨድ የተሰበሰቡ ሰዎች ከመሬቱ አንድ ጫፍ ወደ ሌላኛዉ ጫፍ በአንዴ የሚወጡት ወይም ይዘዉት የሚሄዱት መስመር ነዉ፡፡ እመሙ ሰፊ ወይም ጠባብ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚወሰነዉ በአራሚዎች አልያም በአጫጆች ቁጥር ነዉ፡፡