http://twondifraw.blogspot.com/

Thursday, June 29, 2017

ነገረ-ጠላ



ጠላ በሀገራችን ታላቁና በስፋ የምንጠቀመዉ የወግ መጠጥ ነዉ፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የተጠና አይመስለኝም፡፡ ስለጠላ አጠማመቅ ሂደትም ቢሆን የተጻፈ መረጃም የለንም፡፡ እንዲሁ እንኮመኩመዋለን እንጅ፡፡ እንደማንኛዉም አፍሪካዊ ሀገር ሁሉ አብዛኛዉ የሀገራችን ታሪክ ያልተጻፈና በስነ ቃል ደረጃ የሚገኝ ነዉ፡፡ ጠላም ባይጻፍለትም ስለ የት መጣሹ በታላላቅ አባቶቻችን መካከል የሚነገር ስነ ቃል አለ፡፡ እስኪ በስነቃል ደረጃ ያለዉን ነገረ ጠላ እንይ፡፡ በድሮ ዘመን ሀገረ ገዢዉ ንጉሱ በስልጣኑ ላይ ይነሱብኛል ብሎ የሚፈራቸዉን መኮንኖች ማስገደል ያስባል፡፡ ከዚያም ሚስቶቻቸዉን ይሰበስብና ባሎቻቸዉን እንዲገድሉ እንዲህ ላደረጉም ንግስት አድርጎ እንደሚሾማቸዉና እንደሚሸልማቸዉ ቃል ይገባላቸዋል፡፡ ከሁሉም ሴቶች የተሳካላት አንዲት ብቻ ነበረች፡፡ ንጉሱም ታማኝ መኮንኖቹን ሰብስቦ ባሉዋን እንዴት መግደል እንደቻለች በቤተ መንግስቱ አስጠርቶ ያችን ሴት ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም ያደረገችዉን አንድ በአንድ መለሰች፡፡ መጠጥ አጠጥቼ ከሰከረ በሁዋላ እንደተኛ አናቱን ብየ ገደልኩትና ራሱን ቆርጨ ለእስዎ አመጠውሎዎት ስትል ቃሉዋን ትሰጣለች፡፡ ንጉሱም ዉለታ የዋለለትን መጠጥ ማወቅ ፈለገና መጠጡን አዘጋጅታ እንድታመጣ ያዝዛታል፡፡ ሴቲቱም በሌላ ቀን አዘጋጅታ ታመጣለች፡፡ ንጉሱ በቤተ መንግስታቸዉ ሰገነት ላይ ተቀምጠዉ ከመኮነኖቻዉ ጋር ሲኮመኩሙ ሞቅ ይላቸዋና በመጨረሻም ይሰክራሉ፡፡ ሆድ ያባዉን ጀሾ ያወጠዋል እንደሚባለዉ ንጉሱ በእሳሳቸዉ ትእዛዝ ባል በሚስቱ መገደሉ ቆጭቷቸዉ ነሮረ በስካር ስሜት ዉስጥ እያሉ አንድ ነገር ተናገሩ፡፡ በእዉነት ባልሽን ያስገደለ ይህን መጠጥ ጠላነዉ አሉ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ያ መጠጥ ጠላ ተብሎ እንደተጠራ ቀረ፡፡  

ይህ እንግዲህ በስነቃል ደረጃ ያለ የጠላ አሰያየምና አመጣጥን የሚያስረዳ መረጃ ነዉ፡፡ እስኪ ስለጠላ ዉስን ቢሆንም እንኳ የተጻፉ ማስረጃዎችን እንይ፡፡ ከቀደምት ስራዎች ዉስጥ ስለጠላ የተጻፈ ነገር የምናገኘዉ በንጉስ ዘረ ያዕቆብ ዜና መዋእል ዉስጥ ነዉ፡፡ በቤተ መንግስቱ ዉስጥ ንጉሱን የሚያገለግሉ ደብተሮች ነበሩ፡፡ እነሱም በቅዳሴዉ፣ በማህሌቱ፣ በሰአታቱ በተሾመላቸዉ አቃቤ ሰአት ኣዛዥነት ይተጉ የነበሩ ናቸዉ፡፡ ምግባቸዉም ከቤተ መንግስት ነበር፡፡ ዜና መዋእሉ እንደሚስረዳን፡፡
ለግብር የሚቀርበዉ እንጀራና ጠጅ የሚመጣዉ ከቤተ ፈጣጋር ከግራዋ በአለተሀት (ከግራዋ ልእልት) ከቀኝና ከግራ ካለዉ ግብር ቤት ነበር፡፡ ከንጉሱ በቀር ቀረበዉን የማእድ ብዛት ቁጥሩን ወይም ብዛቱን ማንም አያዉቅም፡፡ አንዱ የጠላ አይነት ጽሩይ ጠላ (የጠራ ጠላ) ይባላል፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ኢታርፍድ ሶስተኛዉ ደግሞ ጸላ ሐጼ ወይም (የአጤ ጠላ) ይባላል፡፡ ይህን ጸላ ሀጼ ንጉሱ በቃላቸዉ ካላዘዙ አይሰጡም፡፡

ከዚህ ዜና መዋእል የምንረዳዉ ከዚያ በፊት ያለዉን ባናዉቅም በሀገራችን በንጉስ ዘርዓ ያእቆብ ዘመን (1434-1468) ጠላ ይጠጣ እንደነበር ነዉ፡፡ ይህም ጠላ በትንሹ ከአምስት መቶ አመት በላይ ያስቆጠረ ድንቅ ባህላዊ መጠጣችን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ ትዉፊቱን ጠብቆ ከእኛ ዘመን የደረሰዉ መጠጥ ከስነቃሉ እንደተረዳነዉ ጠላ ተብሎ ስያሜዉን ያገኘዉ  ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በፊት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ የዘሬን አያድርገዉና በወቅቱ ጠላ እንደ ጠጅ በደረጃ የሚወርድ መሆኑም ከዜና መዋእሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ንጉሱም በስማቸዉ የተጠመቀ ጠላ እንዳላቸዉና ከእሳቸዉ ዉጭ ማንም እንደማይጠጣ እንካን ለሌላ ሰዉ ለራሳቸዉም ቢሆን ራሳቸዉ በቃላቸዉ ካላዘዙ እንደማይመጣላቸዉ ስናይ ጠላ ምን ያህል የተከበረ መጠጥ እንደነበር እንረዳለን፡፡













No comments:

Post a Comment