http://twondifraw.blogspot.com/

Friday, October 19, 2018

ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል

አባባል ትልቅ ሀብት ነዉ፡፡ ሰዉን በአጭር መንገድ ቶሎ ያግባባል፡፡ አብዛኛዎች አባባሎች ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ ናቸዉና ትዉፊታቸዉን ጠብቀዉ ሊሄዱ መልእክታቸዉ ሳይዛባ ሊነገሩና ሊጠበቁ ይገባል፡፡ አንዳንዴ ግን አንዳንድ አባባሎችን ትክክለኛዉን መልእክታቸዉን ገልብጠን ስንረዳቸዉና ስንጠቀምባቸዉ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህ ትክክለኛ  መልእክታቸዉ ተገልብጦ ከሚነገሩ አባባሎች መካከል አንዱ ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀድዶ ይሰፋል ነዉ፡፡ ይህ አባባል የምንኩስና ህይወትን በተመለከተ የሚነገር ነዉ፡፡ምንኩስና የሰዉን ልጅ ከሰማያዉያን መላእክት ጋር አንድ የሚያደርግ በፈቃድ የሚቀበሉት ታለቅ ተጋድሎ ያለበት ክብር ነዉ፡፡ ከመላእክት ጋር የሚያመሳስለዉም አንድ በምንኩስና ህይወት ዉስጥ ያለ ሰዉ የዘወትር ስራዉ እስከ ጊዜ ጥሪዉ ድርስ እንደመላእክቱ 24 ሰዓት በጾም በጸሎትና በምስጋና ፈጣሪዉን ማገልገል ብቻ ስለሆነ ነዉ፡፡ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ በደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሀፋቸዉ ገጽ 64 የህዳግ ማስታወሻቸዉ ላይ ስለ ምንኩስና ያሰፈሩትን እንይ፡፡

አንድ ሊመነኩስ የፈቀደ ሰዉ መጀመርያ በፈቃዱ ከአለም መለየቱን ከዚያም የምንኩስና ኑሮዉ ምን እንደሚመስል የሚያስረዳ ጽሁፍ ያነቡለታል፡፡ በእግዚአብሄርና በሰዉ ፊት ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲስማማ ከፊታቸዉ ያጋድሙትና የጠጉር ልጪት፣ ቀጥሎ ለምንኩስናዉ በሚሆን ልብሱ በሰዉየዉም ላይ እንደሞተ ሰዉ ጸሎተ ፍትሀት ይጸልያሉ፡፡ ከዚያ በሁኋላ መጀመርያ መምህሩ (የገዳሙ አበምኔት) ቀጥሎ በፍትሀቱ የተካፈለዉ ሁሉ ይባርከዉና ያለብሱታል፡፡ የመጨረሻዉ ጸሎት ተጸልዮለት የምንኩስናዉን ህይወት ይጀምራል፡፡ እንደህጉ ቢሆን ከጥቂት አመታት በኋላ ደግሞ አስኬማ የሚባል ልዩ ልብስ ይሰጠዉና ወደ ከፍተኛዉ ደረጃ ይሻገራል፡፡ አስኬማ ከነት የሚሰራ 12 የመስቀል ምልክት ያለበት ቆዳ ነዉ፡፡ እንደ ህጉ ቢሆን ከአስኬማ በኋላ መነኩሴ ከገዳም አይወጣም፡፡ የመጀመርያዉን አስኬማ ለመጀመርያዉ መነኩሴ ለአባ እንጦንስ የሰጠዉ መልአኩ ስለሆነ ልብሱ አስኬማ መላአክት (የመላክት ልብስ) ይባላል፡፡ መነኮሳቱም የምድር ላይ መላአክት ይባላሉ፡፡ አሁን ግን የመነኮሳቱን ልብስ አስኬማ ይሉታል፡፡

ምንኩስና የክብሩን ያህል ጋሩም እጅግ ብዙ ነዉ፡፡ አሁን ማተኮር የሚያሻዉ ጋሩ ወይም መከራዉ ላይ ነዉ፡፡ ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል የሚለዉ አባባል የምንኩስናጋሩን የሚያሳይ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊ ቢሂል ስለሆነ ጋሩን ስንተነትን ብሂሉ ምን እንደሆነ በደንብ ይገባናል፡፡አንዳንድ ሰዎች ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል ሲባል መነኩሴ ስራ ስለሌለዉ ዝም ብሎ ቁጭ ከሚል ቆቡን ቀዶ መስፋት የሚወድ የሚመስላቸዉ አሉ፡፡ አባባሉ የሚነገረዉ ግን በተቃራኒዉ ስራ ለበዛበት እና ባተሌ ለሆነ መነኩሴ ነዉ፡፡ እንዴት እንደሆነ በዝርዝር እንይ፡፡ አንድ መነኩሴ በማህበር በገዳም ወይም በተባትሆ በበርሀ ሲኖር ህይወቱ በሙሉ ለ24 ሰዓት ምስጋና የተሰጠች ናት፡፡ ይህም የምስጋና ህይወት መነኮሱ በግሉ ከአመት እስከ አመት የሚደረሱ የ7 ሰዓት የእየለቱ ጸሎቶችን ይይዛል፡፡ ህይወቱ ዘወትር በዚህ የተጠመደቸ ናት፡፡ በማህበርም ከአመት እስከ አመት የማይታጎለዉ ቅዳሴዉ፣ ኪዳኑ፣ ማህሌቱ፣ ሰአታቱ ሌላኛዉ የምስጋና ህይወት ነዉ፡፡ ከምስጋና ህይወት በተጨማሪ የአንድ መነኮስ ህይወት እድሜ ዘመኑን በስራ የተጠመደች ናት፡፡ በገዳም ያለ መነኩሴ ቅዱሳት መጽሀፍትን ዘወትር ማንበብ ይጠበቅበታል፡፡ መጽሀፈ መነኮሳትን፣ መጽሀፍ ቅዱስን፣ ገድላትን ተአምራትን ያነባል ይተረጉማል፡፡ በእኛ ሀገር በተለይ የመነኮሳት ስራ እጅግ የበረታ እንደነበር የቅዱሳን አባቶቻችንን ገድል ማየት እንችላለን፡፡ በመካከለኛዉ ዘመን የነበሩ መነኮሳት ከአንድ ጉባኤ ትምህርት ሲጨርሱ እንደዛሬዉ በቃል ብቻ ማስመስከር አይጠበቅባቸዉም፡፡ ይልቁንም በቃል ያስመሰከሩትን ትምህርት ብራና ፍቀዉ፣ ሌጦ አዘጋጅተዉ ይደጉሱና ብእር ቀርጸዉ የብራና ጽሁፍ ያዘጋጃሉ፡፡ ለዚህ ነበር የመነኮሳት መፍለቅያ የነበረዉ የአባ ኢየሱስ ሞአ ገዳም የኢትዮጵያ የስነ መለኮት ዩንቨርስቲ የሚባለዉ፡፡ እኒህ መነኮሳት ከዚህ በኋላ ለሌላ ትልቅ ተጋድሎ ራሳቸዉን ያዘጋጃሉ፡፡ እግዚአብሄር በፈቀደላቸዉ ገዳም ሲኖሩ የዘወትር መንፈሳዊ ስራዎቻቸዉን ከፈጸሙ በኋላ ፍጹም ተዋርዶና ትህትና ድካምንም ለሚጠይቅ የጉልበት አገልግሎት ይሯሯጣሉ፡፡

እንበለ ስጋ ኢትቀዉም ነፍስ ነዉና መጽሀፉ የሚለዉ መነኮሳት ለስጋቸዉ መጠገኛ ለሚመገቡዋት ትንሽ /ኩርማን ዳቤ ብዙ ይደክማሉ፡፡ ለዚህም አንድ የገዳም ረድ የሆነ መነኩሴ ዳቤ የሚጋገረዉን እህል በእጅ ወፍጮ ይፈጫል፡፡ ወፍጮ የሚፈጨዉ ተጎንብሶ ስለሆነ በስግደት የደከመን ወገብና የእጅ መገጣጠምያ እጅግ ይፈትናል፡፡ የፈጨዉን ዱቄት ያቦካል ይጋግራል፡፡ ከወንዝም ወርዶ ዉሃ በማሰሮ ቀድቶ በትክሻዉ ተሸክሞ ያመላልሳል፡፡ ይህ መነኮስ ዳቤዉን ከመጋገሩ በፊት ማገዶ ያስፈልገዋልና ወደ በርሃ በመዉረድ እንጨት ቆርጦ ፈልጦ ተሸክሞ ለገዳሙ ማምጣት አለበት፡፡ የፈለጠዉን እንጨት ማገዶ በጢሱም በእሳቱም እየተገረፈ መነኮሳትን አብስሎ ይመግባል፡፡ ከዚያም ለመቅደሱ ዉስጥ አገልግሎት የሚሆ ነገሮችን በማዘጋጀት ጣሩና ጋሩ ይቀጥላል፡፡ ግብር ያደቃል፣ ህብስቱን ይጋግራል፣ ወይኑን ይጠምቃል፣ ፍህም ያያይዛል፡፡ ከዚህ ድካም ሁሉ በኋላ ወደ ህያዉና እዉነተኛዉ ሰማያዊዉ አገልግሎት ይመለሳል፡፡ በትህትናና በለቅሶ በአንቃዶ ህሊና ቅድመ እግዚአብሄር ቁሞ እግሩን ሳያጥፍ ይቀድሳል፣ ያወድሳል፣ ይጸልያል፡፡ ከጸሎት ቀጥሎ ወዙ እስኪንጠፈጠፈ ጣቶቹና ጉልበቶቹ እዥ እስኪወርዳቸዉ ድረስ ይሰግዳል፡፡ ለድካመ ስጋዉ አረፍ ባለበትም ቅዱሳት መጽሀፍትን ያነባል፡፡

ይህ ምድራዊ መልአክ መነኩሴ አደለም የእረፍት ሰዓት ማግኘት ቀርቶ ስለረፍት እንኳን የሚያስብበት ጊዜ የለዉም፡፡ ሆኖም ግን ስራዉን በጊዜ ጨርሶ ምንም የሚሰራ ስራ ጠፍቶ መነኩሴዉ እንደሚቦዝን ቀድሞ ካወቀ ከላይ ያልነዉ የኢትዮጵያዉያንን አባባል ስራ ላይ ያዉላል፡፡ መነኩሴዉ ቆቡን ቀዶ መስፋት ይጀምራል፡፡ ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል ማለት ቆብን ቀዶ መስፋት ለመነኩሴ ስራ ሆኖ ሳይሆን እራስን ከዝርዉነት ለመጠበቅ የሚያደርገዉ ሌላኛዉ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ክፍል ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ ሰዉ ሰራሽ ህግ ሳይሆን ከፈጣሪ የተሰጠ ራስን ከፈተና የመታደጊያ መንገድ ነዉ፡፡ በግብጽ በርሃ ይኖር የነበረዉ የመጀመርያዉ ባህታዊ አባ ጳዉሊ ከፈጣሪዉ ይህ ስራ ተሰጥቶታል፡፡ አባ ጳዉሊ በብህትዉና ሲኖር ሌትም ቀንም አምላኩን እያመሰገነ በትግሀ ጸሎት ነበር፡፡ አባ ጳዉሊ ጸሎት አድርሶ ሲጨርስና አእምሮዉ ሲያርፍ ሰይጣን የአለምን ሀሳብ እያመጣ ጥሎት የመጣዉን ከንቱ ህይወት እያሳሰበ እንዳይፈትነዉ እግዚአብሄር መለአኩን ይልክለታል፡፡ መለአኩም ይመጣና ከበርሀ የበቀሉትን የዘንባባ ቅጠል እየፈተለ ምንጣፍ እየሰራ ያሳየዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አባ ጳዉሊ ከጸሎት በኋላ ስራ ሳይፈታ ሁሌም የዘንባባ ቅጠል በመጠቅለል ምንጣፍ ይሰራ ነበር፡፡ ልብሱም በእለተ እረፍቱ አካባቢ ከቅዱስ እንጦስ ጋር ተገናኝቶ የኮፕት መነኮሳት ልብስ የሆነዉንና አባ ጳዉሊም የኮፕት ቤ/ክ ስርአት ተገዥ መሆኑን ለማስመስከር  ምልክት ይሆነዉ ዘነድ የምንኩስናን ልብስ ከእንጦንስ እስኪቀበል ድረስ ከቅጠል የተሰራ ቀሚስ ነበር፡፡

ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል የሚለዉ ብሂል ለስራ አጥ መነኩሴ ወይም መነኩሴ ስራ የለዉም ለማለት የነተነገረ የሚመስለን ሰዎች ካለን አሁን በእኛ ዘመን ከምናየዉ ሁናቴ የአንዳንድ መነኩሴ ሳይሆኑ ግን መስለዉ ከሚኖሩ ሰዎች እየተነሳን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም  ዛሬ ላይ እንኳን ቆቡን ቀዶ የሚሰፋ ትጉህ መነኩሴ የተሰፋ ቆብ በትክክል የሚያደርግ መነኩሴ የለም፡፡ በትክክል የሚያደርግ ስል ሳያዛንፍ ማለቴ እንዳልሆነና የምንኩስና ቆብ ትርጉሙን በትክክል የተረዳ፣ ከነማን እንደተጫነለትና ለምን እንደተጫነለት ማለቴ ነዉ፡፡ በመካከለኛዉ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያዉያን መነኮሳት እኮ ሲመነኩሱ ብዙ ዉጣ ዉረድ የሚያስጉዝ መንገድ ካለበት ገዳም የሚኖር አባት አፈላልገዉ ሄደዉ ይቀበላሉ፡፡ ለዛዉም ይገባኛል ብለዉ ሳይሆን በአባቶች ተገፋፍተዉ አልያ አምላካቸዉ በራእይ ነግሯቸዉ ነዉ፡፡ አስኬማዉን እና ቅንዋቱን  ደግሞ ከሌላ ተጋድሎ በኋላ እንዲሁ አምላክ ከፈቀደላቸዉ አባት በትህትናና ራስን በማዋረድ እጅ ነስተዉ ይቀበላሉ፡፡ ዛሬ ምንኩስናን አንድ ሰዉ እንዴት ይሆን የሚቀበለዉ? በመካከለኛዉ ዘመን ይኖር የነበረዉ አባ እስጢፋኖስ እንዲህ እንደዛሬዉ ዘመን ምኩስናን ተቀብለዉ በህጉና በስርአቱ ያልተጉዋዙትን አባቶች ነን የሚሉትን እንዲህ ገስጾዋቸዋል፡፡

እነሱስ ቢሆኑ ራሳቸዉን ለአባቶቻቸን ለቅዱሳን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸዉ ለመነኮሳት አባቶች ለእንጦንዮስና ለመቃርዮስ ትእዛዝ ሳያስገዙ የአባትነት ስም እንዴት ወለዱ?  እዉነትን የሚፈልገዉን በከንቱ የሚቃወሙ ከሆነ እኔ ደግሞ ወይ የእግዚአብሄር ወይ የእግዚአብሄር ባሮች ሁኑ እላቸዋለሁ፡፡
ዛሬም በዘመናችን የቤተክርስትያን ዘቦች ይሆናሉ ተብለዉ አለምን ንቀናል ምድራዊ መለአክ ሆነናል ብለዉ የመነኮሱ ሰዎች በስልጣንና በነዋይ ጥም ተነድፈዉ እዉነት ፈላጊ የዋህ ምእመናንን ከመንገድ ሲያስወጡ የቤቴክርስትያንን ህግና ቀኖነዋን ሲንዱ ይገኛሉ፡፡ ታድያ ያ አባባል ለእንዲህ አይነት መነኩሴዎች የተነገረ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ስራ ፈት መነኮሳት በበዙበት ዘመን እማ ብሂሉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡
ቆቡን ቀዶ የሚሰፋ፣
መነኩሴ  እኮ ዛሬ ጠፋ፡፡











3 comments:

  1. እጅግ የሚጥም እና ትልቅ መልእክት ያለዉ ፅሁፍ።

    ReplyDelete
    Replies
    1. አዎ ሁላችንንም ያስተምራል ብየ አስባለሁ።

      Delete
    2. አዎ በደንብ ነው የሚያስተምር ፣ ለስንት ሰዎች መሰለህ እኔ እንኳን እያስተማርኩ ያለሁት

      ምስጋና ይገባሃል

      Delete