መምህር የሚለዉ ስም ከድንጋይ ይከብዳል፡፡ በመጀመርያ ይህ ስም ወንጌል ደጋግሞ እንደሚነግረን የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠርያ ነዉ፡፡ ስለዚህ ማንኛዉም ፍጡራን ሊሸከሙት አይቻላቸዉም፡፡ ሲቀጥል ራሳቸዉን ክደዉ መስቀሉን ተሸክመዉ መድሀኔአለምን የተከተሉት የሀዋርያት መጠርያ ነዉ፡፡ በሁዋላም መናፍቃንን ድል የነሱ አንገታቸዉን ለሰይፍ የሰጡ መንበራቸዉን ትተዉ የተሰደዱት የሊቃዉንት መጠርያ ነዉ መምህር የሚለዉ ከባዱ ስም፡፡ መሬት ሲያረጅ ጃርት ያፈራል እንዲሉ ቤተክርስትያን ባታረጅም ዛሬ ዛሬ በዙርያዋ ጃርቶች መፈልፈላቸዉ አልቀረም፡፡ እናም ጃርቶች መምህራን እየተባሉ መጠራት ጀመሩ፡፡ በዚህ ዘመን በቤተክርስትያናችን አንድ ሰዉ መምህር ነኝ ብሎ በእነዮሀንስ አፈወርቅ፣ቄርሎስ፣ አትናቴዎስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በቆሙበት አዉደ ምህረት ቆሞ ለማስተማር በጉባኤያቸዉም ተቀምጦ ለማስቀጸል ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ያሟላ መሆን ይገባዋል፡፡
1. በመምህርነት ሙያ ያስመሰከረ 2. ባይማርም በእግዚአብሄር የተመረጠ
እግዚአብሄር በማይመረመር ጥበቡ ከታናናሾች መካከል ከሚመርጠዉ መምህር ዉጭ (ይህም በደጋጎች ዘመን ነበር) በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን መምህር ለመሆን መንገዱ አንድ ብቻ ነዉ፡፡ እርሱም ቤተክርስትያናችን ካሉዋት አራቱ ጉባኤያት ማለትም አቋቋም፣ ቅኔ፣ ዜማነና መጽሀፍ ቤት በመጨረሻዉ እርሱም በመጽሀፍ ቤት ጉባኤ ገብቶ ጠንቅቆ ተምሮ ምስጢር አደላድሎ ያስመሰከረ መሆን አለበት፡፡ ይህ ለአዉደምህረት አገልግሎት ብቻ ነዉ፡፡ በቤተክርስትያናችንም መምህር የሚባሉ ሰዎች ከሚከተሉት ሙያዎች በአንዱ፣ በሁለቱ አልያም በሁሉም ያስመሰከሩ መሆንም አለባቸዉ፡፡
የቅኔ መምህር፣የአቋቋም መምህር፣የዜማ መምህር፣የመጽሀፍ መምህር፡፡ በእነዚህ ሙያዎች ሳያስመሰክር መምህር ተብሎ በአዉደ ምህረት የሚቆም ሰዉ ትንቢቱ የተነገረበት ሰዉ ይመስላል፡፡ አንድ በቤተክርስትያን መምህር ተብሎ የሚጠራ ሰዉ ከእዉቀቱ በተጨማሪ ክህነት ሊኖረዉ ይገባል፡፡ በወንጌል በጎቼን ጠብቅ፣እንዲሁም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸዉ የተባሉት ካህናት ናቸዉና፡፡
ወደ ቀደመዉ ነገር እንመለስና አንድ በቤተክርስትያናችን መምህር የሚሆን ሰዉ ወደ መጽሀፍ ቤት ጉባኤ ከመሄዱ በፊት የሚጠበቁበት ሁለት አበይት ቁም ነገሮች አሉ፡፡ ስለ እነዚህ ቁም ነገሮችና አጠቃላይ ስለ መጽሀፍ ቤት ጉባኤ ምንነት ሳነብ ካገኘዉት መረጃዎችን ከቤተክርስትያን ሰብስቦ ጥናት የተደረገበትን የአንድ ታላቅ መጽሀፍ ዳሰሳን እንደሚከተለዉ አስፍሬዋለሁ፡፡
Two of the requirements for going to Metshaf bet are knowledge of qene and proficiency in Ge’ez. Metshaf bet has four Gubae;
1. New Testament takes 4-5 years to complete with its 35 books.
2. Old Testament takes 6-7 years to complete its 46 books
3. Book of Liqawuint takes 6-8 years
4. Books of Monks the study of the life of monks takes 3-4 years
It would take a student 19-21 years to complete Metsehafe bet. This did not include the time the student spent at Nibab Zema and Qene bet.
ከላይ እንደሚነበበዉ መምህር ተብሎ የሚሾም ሰዉ መምህር ከሚያስብለዉ መጽሀፍ ቤት ጉባኤ ከመዝለቁ በፊት ሁለቱ የሚያሟላቸዉ ቁም ነገሮች
1. ቅኔን መጠንቀቅ
2. ግእዝንም ጠንቅቆ ማወቅ ነዉ፡፡
ሙሉ ቅኔን ተምሮ ለመጨረስ ከትንሹ ባለ 2ት ስንኝ ጉባኤ ቃናን እስከ ትልቁ ባለ 12 ስንኝ እጣነ ሞገር ጠንቅቆ መማር ይጠይቀል፡፡ ባጠቃላይ ቅኔን ለመጨረስ እስከ 7 አመት እንደሚፈጅ ሀይማኖታዊ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጸዉ በመጽሀፍ ቤት አራት ጉባኤያት አሉ፡፡ አንድ መምሀር ቢችል ሙሉዉን መማር አለበት፡፡ እርሱም አራት አይና ተብሎ ለቤተክርስትያን በሁሉም የሙያ መስክ የሚጠመድ በሬ ይሆናል፡፡ ካልሆነም ቢያንስ አንዱን ጉባኤ መጠንቀቅ አለበት፡፡ አንድ በአንድ እንይ፡፡
መጽሀፈ አዲሳት፡ የሀዲሳት መምህር ለመሆን ከ4-5 አመት መማር አለበት፡፡ በዚህም ቆይታዉ 35 መጽሀፍትን ተምሮ ይጠነቅቅና ለሀዲሳቱ አንገቱን አስከመስጠት ተጠያቂና ምስክር ይሆናል፡፡ ይህን ጠንቅቆ አስመስካሪዉ መምህሩ መምህር ብሎ ሲሾመዉ ያስመሰከረበትን ሙያ የሚገልጽ ማእረግ አብሮ ይሰጠዋል፡፡ መጋቢ ሀዲስ የሚል፡፡ መምህሩ ግን ያፈራዉን እዉቀት በህይወት/በተግባር መኖሩን ገና ሳያዉቅ በዚህ ማእረግ ቢገባዉም እንኩዋን ሊጠራበት አይወድም፡፡
መጽሀፈ ብሉያት፡ አንድ ሰዉ የብሉያት መምህር ለመሆን ከ6-7 አመት በጉባኤ መማር አለበት፡፡ በዚህም ቆይታዉ 46 መጽሀፍትን ተምሮ ሚስጥራትን ጠንቅቆ ይወጣል፡፡ እንደሀዲሳቱ ሁሉ ለብሉዩም መምህር የሙያ ማእረግ መጋቢ ብሉያት ተብሎ ያስመሰክራል
መጽሀፈ ሊቃዉንት፡ ስለእቅበተ ሀይማኖት፣ ዶግማ መምህር ለመሆን ከ6-8 አመት ይማራል፡፡ በዚህም ሀይማኖተ አበዉን፣ የእነቅዱስ ቄርሎስ፣ አትናትዮስ፣ ባስልዮስ ጎርጎርዮስ ዮሀንስ አፈወርቅ፣ ኤፍሬምና ሌሎች ታላቅ አባቶችን ድርሳን ይጠነቅቃል፡፡ በተጨማሪም ፍትሀ ነገስቱን ባህረ ሀሳቡን ፌሳሎጎስን (ስለ እንስሳትና እጽዋት የሚያጠና) ያስሄዳል፡፡ ሲጠነቅቅም ሊቀሊቃዉንት በሚል የማእረግ ስም ያስመሰክራል፡፡
መጽሀፈ መነኮሳት፡ አንድ የመጽሀፈ መነኮሳት መምህር የሚሆን ሰዉ ከ3-4 አመት በጉባኤ መማር አለበት በዚህም ቆይታዉ ሶስቱን መጽህፈ መነኮሳት ይጠነቅቃል፡፡
በአጠቃላይ ከእግዚአብሄር በታች ለቤተክርስትያን ዋልታ እና መከታ የሚሆን አንድ ሰዉ በመጀመርያ ለጌታችን ቀጥሎ ለሀዋርያቱ የተሰጠዉን ሊሸከሙት የማይቻለዉን ከባዱን ስም ‘’መምህር’’ን ለመሸከም ከ19-21 ዓመት መማር አለበት፡፡ ይህም አስቀድሞ ቅኔን ለመማር የሚፈጀዉን 7 አመት ሳንጨምር ነዉ፡፡
የዛሬ መምህሮቻችን በእዉኑ መምህራነ ወንጌል ናቸዉን?
ይህን የምንመዝነዉ በእኛ አእምሮ ያይደለ በመጽሀፍት መለኪያነት ነዉ፡፡ መጽሀፍት በቤተክርስትያናችን አንድ ሰዉ መምህር እንዴት እንደሚሆንም ሲማር የት በማን ሲማር እንደሆነ ጠንቅቀዉ ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህ ሚዛንነት የዛሬ መምህሮቻችንን ብንለካቸዉ ምን ይመስሉ ይሆን፡፡
ዛሬ ላይ ቴዎሎጂ የሚባል ዘመናዊ ት/ትቤት ተከፍቱዋል፡፡ በእዉነቱ እነዚህ ት/ትቤቶች ኢትዮጲያዊ ትዉፊትን የጠበቁ እዉነተኛ መምህሮቻችንን ያስገኝልናልን? በመጽሀፉ መሰረት በመጽሀፍ ጉባኤ ቤት የተማሩት መምህሮቻችን ጥሬ አልያም ኮቸሮ እየቆረጠሙ ከአለም ተለይተዉ በጾምና በጸሎት ተጠምደዉ ነዉ፡፡ በቲዎሎጂ ዘመናዊ ት/ትቤት የተማሩት ደግሞ በኤክስቴንሽን ነዉ የተማሩት፡፡ እርሱም በአለም ስራቸዉ ሀጥያትም ይሁን ጽድቅ ሲወጡ ሲወርዱ ቆይተዉ በትርፍ ጊዜያቸዉ የሚማሩት ነዉ፡፡ መለኮታዊዉን የእግዚአብሄር ቃል ተምሮ መምህር ሆኖ ለማስተማር ተበልቶ ተጠጥቶ ሆድ ሲሞላ ደረት ሲቀላ የሚያስተምር ቴዎሎጂ እዉነተኛ መምህራንን ያፈራ ይሆን፡፡ መምህሮቻቸዉም በነጻ የሰጠዋችሁን በነጻ ስጡ የሚለዉን ቃል ንቀዉ በገንዘብ በደሞዝ አይደለምን የሚያስተምሩት፡፡ ተማሪዉም የእግዚአብሄርን ቃል በገንዘብ ይገዛል፡፡ ሲመረቁም ገንዘባቸዉን ለማስመለስ ይመስላል መጽሀፍ ጻፍን ብለዉ፣ ካሴት አሳተምን በማለት ቀጥታ ወደ ንግዱ ይገባሉ፡፡ ለዛዉም የእግዚአብሄርን ቃል፡፡ በኒህ ተማሪዎች አልፈርድባቸዉም፡፡ መምህሮቻቸዉ ያሳዩዋቸዉን ነዉና የተከተሉት፡፡ ቀድሞ መልካም መምህር መምረጥ ግዴታቸዉ ነበረርና ከመጠየቅ ግን አይድኑም፡፡
ሁሉም ይሁን ሆኗልም ቤተክርስትያንን የሚያሳፍራት ግን መምህር ተብለዉ ሲጠሩ፣ ተጠርተዉም በአዉደምህረት ሲቆሙ እነሱም ይገባናል ብለዉ ሲቀበሉት ነዉ፡፡ እንደእዉነተኞች መምህራኖቻችን ቅኔን ጠንቅቀዉ ይሆን፣ ግእዙ ገብቱዋቸዉ ይሆን፣ እሽ የየትኛዉስ መጸሀፍ መምህር ናቸዉ፡፡ የሀዲስ፣የብሉይ፣የሊቃዉንት፣የመነኮሳት፣የአቋቋም፣የቅኔ፣የዜማ፣በእነዚህ ጉባኤያት ስንት አመት ተማሩ፡፡ መልሱ አልቦ ነዉ፡፡ የአንዱም ስላልሆኑ ሲያስተምሩ ካስተዋላችሁ ርእሱ ከአንዱ መጽሀፍ ተመርጦ ሳለ የማይነካኩት ጥቅስ፣የማይዳስሱት መጽሀፍ የለም፡፡ ትምህርታቸዉም እንደአለማዉያን ሁሉ እዉቀታቸዉን እንጅ ህይወታቸዉን አይደለም የሚገልጸዉ፡፡ እዉቀት የተማረ ምእመን ደግሞ ምን እንደሚመስል አቡነ ሽኖዳ እንዲህ ብለዉናል፡፡ የሚያስተምርህ መምህር እዉቀቱን ከሆነ ሊቅ ትሆናለህ ህይወቱን ከሆነ ደግሞ ክርስትያን ትሆናለህ ይላል፡፡ ለነገሩ የዛሬ ዘመንም ምእመን እዉቀት ስለሆነ የሚሻ ሰይጣን አመቻችቶለታል፡፡ ለምእመኑስ እንደ አርዮስ ሊቅ ሆኖ ሲኦል ከመወርድ እንደ አላዛር ድሀ ሆኖ በአብርሀም እቅፍ መኖር ለዉድድር ሚቀርብ ሀሳብ ይሆንን
የዛሬ መምህሮቻችን የትኛዉን መጻፍ እንዳስመሰከሩና የየትኛዉ መምህር እንደሆኑ ቢለዩልን ምናለ፡፡ ስንት አመት ተምረዉ ነዉ ከየትኛዉ ጉባኤና መምህርስ አስመስክረዉ ነዉ ግሱን፣እርባታቸዉን፣ሰዋሰዉን ጠንቅቀዉ ሳይሆን መጋቢ ሀዲስ፣መጋቢ ብሉይ ወዘተረፈ የሚባሉት፡፡
በኋለኛዉ ዘመን ሀሰተኞች መምህራኖች ይነሳሉ ያለን ትንቢት እነዚህ መምህሮቻችን ሳይሆን ይቀራልን፡፡ እዉነተኛ መምህራን ላለመሆናቸዉ ግብራቸዉ ይናገርባቸዋል እኮ፡፡እንዴት
• እዉነተኛ መምህር የጌታን ወንጌል ላልተዳረሱት ለአረማዉያን አስተምሮ የስላሴን ልጅነት ያሰጣል ካልተቀበሉት ተወግሮ ሰማእትነተን ይቀበላል፡፡ እኛ ግን ካሉን ብዙ መምህር ተብየወቻችን አንዱንም አርያ ሆኖን አላየንም፡፡ የዛሬ መምህር ተብየዎቻችን አዉደ ምህረት ወጥቶ የሌሎችን እምነት ከመንቀፍ በቀር አንድም መምህር በራሱ ተመርቶ እንደ ሀዋርያት እና ሊቃዉንት አባቶቻችን በሚነቅፋቸዉ ሰዎች ጉባኤ ተገኝቶ እስላሙን ያስተማረ ጴንጤዉን እየሰበከ ብሎም የመለሰ የለም፡፡ በእኛዉ በዘመናችን እንኳ እነአያሌዉ ታምሩ አህዛብን እዉነት ካመኑበት ለምን አንነጋገርም እያሉ እዉነተኛ መምህርነታቸዉን ባስመሰከሩበት አዉደ ምህረት ዛሬ ቡችሎች ይፈነጩበታል፡፡
• እኒህ መምህሮቻችን ጩኸታቸዉ ሁሉ አዉደምህረት ላይ ነዉ፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ የጸኑ ክርስትያኖች ናቸዉ ያሉት፡፡ ጩኸታቸዉም ፍሬ አልባ ከመሆኑ የተነሳ አንዳቸም ሊያድን አልቻለም ጭራሽ ምእመናኑን ከማደንዘዝ ዉጭ፡፡ እስኪ ማን ነዉ በእነሱ ተምሮ አለምን ንቆ የመነነዉ፣ ማንነዉ የመነኮሰዉ፣ በእነሱ የተማረ ሰዉ ሀሜተኛ፣ዉሸታም፣አደለም ጠላቱን ወንድሙን የሚጠላ በመቃሙና በማጨሱ የቀጠለ አይደለም የሆኑት፡፡
• ለእናንተስ ምንም አይኑራችሁ የተባሉት መምህራን ወንጌልን በብር (በዉሎ አበል) ያስተምራሉ፡፡ ለማደርያቸዉ የተመቼ ሆቴል ለምግባቸዉ የላመ የጣመ ይጠይቃሉ፡፡ በእዉኑ መምህራኖቻን ከምእመናኑ ይለያሉን፡፡ እንዴት የጳዉሎስና የጴጥሮስ በረከት ሊያድርባቸዉ ይችላል፡፡
ጌታስ እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ ማቴ 23፡8፡፡ የዛሬ ሰባክያን አቤት መምህር ተብለዉ ሲጠሩ የሚሰማቸዉ ፍስሃ አቤት ደስታቸዉ፡፡
5/5/2009