ነገረ-ጠጅ
(የተጣለ መጠጥ)
እነሆ በሀገራችን
መጠጥ ይጣላል (ጠጅ)፣ ይሾማል (ጠጅ)፣ ይበጠበጣል (ጠላ)፣ ይጠመቃል (ጠላ)፣ ይወጣል (አረቂ)፡፡ እኒህን ሀገር በቀል አባት አደር ባህላዊ መጠጦች አንድ የሚያደርጋቸዉ ባህርይ አላቸዉ፡፡ የእኛን ሙሉዉን ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ዘመን አያድርገዉና መጠጦቹ የሚጣልባቸዉ፣ የሚሾምባቸዉ፣ የሚበጠበጥባቸዉ፣
የሚጠመቅባቸዉና የሚወጣባቸዉ እቃዎች ከሸክላ መሰራታቸዉ ነበር፡፡ በኋለኛዉ በእኛ ዘመንማ ቫይረስ ይከላከል ይመስል የላስቲክ እቃ ሁሉ
ሸክላን እየገፈተረ ጥልቅ ማለት ጀመረ፡፡ እኒንያ የሸክላ እቃዎች ማሰሮ፣ እንስራ እና ጋን ናቸዉ፡፡ ጋን ከሸክላ የሚሰራ የወግ እቃ ሲሆን ምናልባትም በሀገራችን ከባህላዊ የቤት ቁሳቁሶች ትልቁ ሳይሆን አይቀርም፡፡በሃገራችን
በነገስታት ዘመን አንድ ታላቅ ጋን እጅግ ማለፍያ የሆነ አገልግሎት ነበረዉ፡፡ እርሱም ለንጉሱና ሹማምንቶቹ የሚሆን ባለሙያ ሴት የጠመቀችዉ ጠጅ መሾምያነት ማገልገል ነበር፡፡ ጠጅ እጅግ የተወደደ የክብር መለክያ የሆነ መጠጥ ስለነበር በከበረ እቃ ማለትም በጋን ተሹሞ ጋኑም በክብር ቦታ ለብቻዉ በእልፍኝ ዉስጥ ይቀመጣል፡፡ ጠጁ በጋን መዘጋጀቱ ከጠጁም ከጋኑም ክብር የተነሳ ጠጁ በ ጋን ተሾመ እሰከመባል ድረስ የሹመት ማእረግ ነበረዉ፡፡ ይህ በጋን የተሾመዉ ጠጅ በንግስናና በምስፍና ለተሸሙት ሰዎች በማእረግ ይወርዳል ይጠጣል፡፡
ዉሎ ዉሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከሞት አይቀርምና ሹመት ይሻራል ንግስናም ይቀራል፡፡ በሀገራችን ንግስና ሲቀር ጠጅም መሾሙ ቀረ፡፡ መጠጣቱ ግን አልቀረም፡፡ ንግስና ከቀረ በኋላ ኢትዮጵያዊት እናት ጠጅ ሾምኩ ሳይሆን የምትለዉ ጠጅ ጣልኩ ነዉ፡፡ እናም አባቶች የነገስታትን ዘር ተዋግተዉ አዳክመዉ ንጉስ በዙፋን መሾም ሲቀር እናቶች ደግሞ ጠጅ በጋን መሾሙን አቁመዉ በሮቶ መጣል ጀመሩ፡፡ እናቶች ጠጅ ጣልኩ ይበሉን እንጅ እንዴት እንደጣሉት ያወቁ አይመስለኝም፡፡ጊዜ ሰጥቷቸዉ እስከዚህ ዘመን የደረሱ የተሾመም የተጣለም ጠጅ የጠጡ አዛዉንት አባቶች እንደሚናገሩት ከሆነ እናቶች ጠጅ መጣል የጀመሩት በሶስት መንገድ ነዉ ይላሉ፡፡
- · ማር ለከለር ብቻ ተጨምሮ ጠጁ በስኳር መጠመቅ ሲጀምር፡
- · ጋን ከእልፍኝ ጠፍቶ ማድቤት በተቀመጠ ጎማ ሲጠመቅ፡፡
- · ለንጉስ ቀርቶ ለህዝብ መዉረድ ሲጀምር ጠጅ መጣሉ ተጀመረ፡፡
ታድያ እኒህ አባቶች ስናገሩ እንደምንሰማዉ ከሆ በሀገራችን የጠጅ ሹመት
ከንግስና ሸረት ጋር አብሮ ከስሞ ቀርቷል፡፡
ከላይ አብረን እንዳየነዉ የተሸመ ጠጅ ደንበኞች የማንም አልፈ ሂየጅ ሳይሆን
ነገስታቱ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱና ልኡላኑ ነበሩ፡፡ የተጣለ ጠጅ ደንበኞችሳ አትሉኝም፡፡ እነሱማ አብዛኛዎቹ ኑሮ የጣላቸዉ የሚመስሉ ሊጠጡ ሲሄዱ ትያትር ሲተዉኑ ቆይተዉ ከመድረክ ወረዱ የሚመስሉ
ናቸዉ፡፡ እንዴት ቢሆን አትሉኝም፡፡ እንዲህ ነዋ፡፡ አለባበሳቸዉንስናይ ከመሃል በእላቂ ካፖርት አልያም ረጅም ጃኬት ዉስጥ የተደበቁ ከታች ባት ከጉልበት በሚሸፍን ቦት ጫማ ገብተዉ የሚንደፋደፉ ከላይ ደግሞ አይንና አፍንጫን አፍና የምትይዝ አሮጊት ኮፍያ ያጠለቁ በእድሜ አባዋራ፣ ወጣትዋራ እና አሁን አሁን ደግሞ እማዋራ የሆኑ ናቸዉ፡፡ እኒህ ዋራዎች አካሄዳቸዉን ስናይ የተጣለዉን ጠጅ ለመጠጣት በእጃቸዉ ሰንጣራ ዘንግ ወይም ከዘራ ተመርኩዘዉ ሰአት አመራረጣቸዉ ደግሞ ጸሀይ ብቅ ወይም ዘቅዘቅ ስትል ማዝገም የሚጀምሩ ናቸዉ፡፡ የሚገርመዉ የአሁኑ ጊዜ ጠጅ መጣሉ ብቻ ሳይሆን መጣሉ (አላልተህ አንብብ) ጭምር ነዉ፡፡ እናም እኒህ የጠጅ ደንበኛ ዋራዎች እንዲህ ከእግር እስከ ራሳቸዉ መልበሳቸዉ ጠጁ እንደሚጥላቸዉ ስላወቁ ነዉ ተብለዉ ይታማሉ፡፡ እንዳይወድቁ ዘንግ ወይም ከዘራ ይመረኮዛሉ፡፡ ዘንጉ አልችላቸዉ ብሎ ከወደቁ ወድቀዉ እንዳይቀሩ ቅልጥማቸዉን በቦት ወገባቸዉን በካፖርትና አናታቸዉን በኮፍያ ከጉዳት ይከላከላሉ፡፡ በተለይ የኮብልሰቶን መንገድ ከመጣ ወዲህ እንዲህ እንዲቀጥሉ አስገድዷቸዋል፡፡ አንድ በማህበረሰባዊ ህይወት ዙሪያ ዳሰሳ እያደረገ በብሎግ ለህብረተሰቡ መረጃ ሚያጋራ ጦማሪ እንዲህ ጦምሮ ነበር፡፡ መንግስት ህዝቡ እንዲወድቅ የቢራ ፋብሪካዎችን ይከፍታል፣ ወድቆ እንዳይነሳ ደግሞ ኮብልሰቶን መንገድ ይሰራል፡፡ የጠጅ ደንበኛ ዋራዎች ግን አልሞት ባይ ተጋዳይ ነቄዎች ስለሆኑ ወድቀዉ እንዳይቀሩ መንግስትን ይፎካከራሉ፡፡
በጃንሆይ ዘመን ከነበሩት ሀገር ወዳድ መኳንንት
መካከል በላይ ዘለቀ የጎጃሙ ጀግና ይገኝበታል፡፡ በላይ ዘለቀ ጠጅ ያሾምበት የነበረዉ ትልቅ ጋን ነበረዉ፡፡ይህ ጋን አሁን በምስራቅ ጎጃም ዞን ልዩ ስሙ ሶማ ከተባለ በርሃማ ቦታ ይገኛል፡፡ ሶማ በርሃ በላይ ዘለቀ ጣልያንን ሲወጋ መሽጎ የነበረበትና በመጨረሻም በጃንሆይ ወታደሮች ተላልፎ የተሰጠችበትእጉም ብሎ የተጠለለባትን ሰዉ አሳልፋ ሰጠች የቦታ ባንዳ ነች፡፡ ታድያ አሁን የበላይ ጋን ጠጅ የሚሾምበት ቀርቶ ጠጅ የሚጥልበት ሰዉ እንኳን ስለጠፋ የዞኑ ቅርስ ሆኖ የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን ተገደደ፡፡ይህን አይነት ታሪክስናገኝ ደግሞ ወደፊት ጠጅ ከነመጣሉ እንኳ እንዳይቀር ያሰጋል፡፡የነጃንሆይ ጋን የት ደርሶ ይሆን፣ የአጼ ሚኒሊክስ ዕንጦጦ ማርያምን ሲያስመርቁ ከጋን ተርፎ ጠጅ ያሾሙበት ጉድጓድ ምን ሆኖ ይሆን?
ጠጅን ስናስብ በጣም የሚያሳዝነዉ ነገር በእጅ ጣት በማትቆጠር እድሜ ዉስጥ ከንጉስ ተላልፎ ለህዝብ መናኘቱ ከእልፍኝ ወጥቶ በገበያ ላይ መዋተቱ ነዉ፡፡ ጠጅ ቸርቻሪዎችም መቸርቸርያዎችም እንደ “ቸርች” ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቡ መምጣት ይዘዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ ጠጅ ቤቶችና የጠጅ ደንበኞች በየሰፈሩ በየጉራንጉሩ የበዙት ለምንድን ነዉ? የሚል፡፡ እኔ ግን
ጠጅ መሾሙ ቀርቶ መጣል ስለጀመረ ነዉ እላለሁ፡፡
የሚያሳስበዉ ነገር ግን ጠጅ መጣሉ አይደለም መሾሙ እንደቀረ መጣሉ ሲቆም ጠጅ ምን እንደሚሆን ነዉ፡፡
አዎ በነገስታ ዘመን ጠጅ አይጣልም ነበር፡፡ ይሾማል እንጅ፡፡ ለተራ ሰዉም
አይሰጥም፡፡ የሚገርመዉ ጠጅ በተራ ሰዉ አለመጠጣቱ ሳይሆን በእንዲህ
አይነት ሰዎች ቤት እንኳን አይሾምም ነበር፡፡ የሾመ ሰዉ ቢገኝ ቅጣት ነበረዉ፡፡ ጠጅ ለመሾም አንድ ሰዉ ማእረግ ያለዉ መሆን ነበረበት፡፡
አይ ጠጅ የነበረዉ ክብር ኖሯል አያ፡፡ እስኪ ይህን ታሪክ በማስረጃ እንይ፡፡
“………… See how our learnd
and pious people lower themselves to an earthly king?” Berhan whispered into my
ear. “one other thing Tewaney, Teji flows like water here but you and I can’t
brew it at home, even if we wanted to, unless such a title such as Landowners
or Kegnazmach or have fought in the flanks of a prince, or killed or captured
enemy. People brew it secretly, though. If they are caught it will be
confiscated and they may even face flogging, I find this truly detestable” (source
Hiwot Teffera, Mine to Win 2016 p.138)
በግርድፉ ሲተረጎም
…………..ብርሀን በጆሮየ
እንዲህ ሲል አንሾካሾከ፡፡ ተመልከት የእኛ ህዝብ ራሱን ለምድራዊዉ ንጉስ እንዴት እንደሚያጎበድድ፡፡ ሌላኛዉ ተጨማሪ ነገር ተዋናይ፣
እዚህ ጠጅ እንደዉሃ ይፈሳል፣ እኔና አንተ ግን በቤታችን መሾም አንችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ማእረግ ማለትም ቀኝ አዘማችነት፣
የመሬት ባላባትነት ከሌለን አልያም ከንጉስ ወታደር ጎን ተሰልፈን ጠላት ካልማረክን ወይም ካልገደልን ጠጅ መሾም ብንፈልግም አንችልም፡፡
ሰዎች ተደብቀዉ ጠጅ ይሾማሉ፡፡ ከተያዙ ግን ጠጁን ይቀማሉ እንዳዉም በጅራፍ ይገረፋሉ፡፡ በእዉነት ለመናገር ይህ ለእኔ አስከፊ
ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ከ Mine to Win መጽሀፍ እንደምንረዳዉ ተዋናይ የቆሎ ተማሪ ሲሆን
በ1857 የእድ ዉሃ አካባቢ ተወልዶ በ1870ዎቹ በደብረ ወርቅ ማርያም
ገዳም ፊደል፣ ንባብ እና ዜማ ተምሯል፡፡ ቀጥሎ ዋሸራ ማርያም በመሄድ ቅኔ ከሊቀ ሊቃዉንት ብርሀነ ሰረገላ ታየ እግር ስር እየተማረ
በነበረበት ወቅት ቀኝአዝማች ሳህለማርያም የሚባል አንድ የመሬት ባላባት ድግስ ጠርቷቸዉ ጠጅ እንደ ዉሃ ሲጠጣ አስተዉሏል፡፡ በዚህ
ወቅት አስተማሪዉ ሊቀ ሊቃዉንት ብርሀነ ስለጠጅ ምንነት በወቅቱ ምን እንደሚመስል ቅኔ በለመደዉ አፋቸዉ አሳምረዉ ለተማሪያቸዉ ተዋነይ
ያስጨበጡት ቁም ነገር ለእኔም ጠጅ ዛሬ እንደተጣለ ያኔ እንዴት እንደተሾመ መጣጥፌ ትልቅ ማስረጃ ሆኖልኛል፡፡