http://twondifraw.blogspot.com/

Thursday, June 29, 2017

ነገረ-ጠላ



ጠላ በሀገራችን ታላቁና በስፋ የምንጠቀመዉ የወግ መጠጥ ነዉ፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የተጠና አይመስለኝም፡፡ ስለጠላ አጠማመቅ ሂደትም ቢሆን የተጻፈ መረጃም የለንም፡፡ እንዲሁ እንኮመኩመዋለን እንጅ፡፡ እንደማንኛዉም አፍሪካዊ ሀገር ሁሉ አብዛኛዉ የሀገራችን ታሪክ ያልተጻፈና በስነ ቃል ደረጃ የሚገኝ ነዉ፡፡ ጠላም ባይጻፍለትም ስለ የት መጣሹ በታላላቅ አባቶቻችን መካከል የሚነገር ስነ ቃል አለ፡፡ እስኪ በስነቃል ደረጃ ያለዉን ነገረ ጠላ እንይ፡፡ በድሮ ዘመን ሀገረ ገዢዉ ንጉሱ በስልጣኑ ላይ ይነሱብኛል ብሎ የሚፈራቸዉን መኮንኖች ማስገደል ያስባል፡፡ ከዚያም ሚስቶቻቸዉን ይሰበስብና ባሎቻቸዉን እንዲገድሉ እንዲህ ላደረጉም ንግስት አድርጎ እንደሚሾማቸዉና እንደሚሸልማቸዉ ቃል ይገባላቸዋል፡፡ ከሁሉም ሴቶች የተሳካላት አንዲት ብቻ ነበረች፡፡ ንጉሱም ታማኝ መኮንኖቹን ሰብስቦ ባሉዋን እንዴት መግደል እንደቻለች በቤተ መንግስቱ አስጠርቶ ያችን ሴት ይጠይቃታል፡፡ እርሱዋም ያደረገችዉን አንድ በአንድ መለሰች፡፡ መጠጥ አጠጥቼ ከሰከረ በሁዋላ እንደተኛ አናቱን ብየ ገደልኩትና ራሱን ቆርጨ ለእስዎ አመጠውሎዎት ስትል ቃሉዋን ትሰጣለች፡፡ ንጉሱም ዉለታ የዋለለትን መጠጥ ማወቅ ፈለገና መጠጡን አዘጋጅታ እንድታመጣ ያዝዛታል፡፡ ሴቲቱም በሌላ ቀን አዘጋጅታ ታመጣለች፡፡ ንጉሱ በቤተ መንግስታቸዉ ሰገነት ላይ ተቀምጠዉ ከመኮነኖቻዉ ጋር ሲኮመኩሙ ሞቅ ይላቸዋና በመጨረሻም ይሰክራሉ፡፡ ሆድ ያባዉን ጀሾ ያወጠዋል እንደሚባለዉ ንጉሱ በእሳሳቸዉ ትእዛዝ ባል በሚስቱ መገደሉ ቆጭቷቸዉ ነሮረ በስካር ስሜት ዉስጥ እያሉ አንድ ነገር ተናገሩ፡፡ በእዉነት ባልሽን ያስገደለ ይህን መጠጥ ጠላነዉ አሉ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ያ መጠጥ ጠላ ተብሎ እንደተጠራ ቀረ፡፡  

ይህ እንግዲህ በስነቃል ደረጃ ያለ የጠላ አሰያየምና አመጣጥን የሚያስረዳ መረጃ ነዉ፡፡ እስኪ ስለጠላ ዉስን ቢሆንም እንኳ የተጻፉ ማስረጃዎችን እንይ፡፡ ከቀደምት ስራዎች ዉስጥ ስለጠላ የተጻፈ ነገር የምናገኘዉ በንጉስ ዘረ ያዕቆብ ዜና መዋእል ዉስጥ ነዉ፡፡ በቤተ መንግስቱ ዉስጥ ንጉሱን የሚያገለግሉ ደብተሮች ነበሩ፡፡ እነሱም በቅዳሴዉ፣ በማህሌቱ፣ በሰአታቱ በተሾመላቸዉ አቃቤ ሰአት ኣዛዥነት ይተጉ የነበሩ ናቸዉ፡፡ ምግባቸዉም ከቤተ መንግስት ነበር፡፡ ዜና መዋእሉ እንደሚስረዳን፡፡
ለግብር የሚቀርበዉ እንጀራና ጠጅ የሚመጣዉ ከቤተ ፈጣጋር ከግራዋ በአለተሀት (ከግራዋ ልእልት) ከቀኝና ከግራ ካለዉ ግብር ቤት ነበር፡፡ ከንጉሱ በቀር ቀረበዉን የማእድ ብዛት ቁጥሩን ወይም ብዛቱን ማንም አያዉቅም፡፡ አንዱ የጠላ አይነት ጽሩይ ጠላ (የጠራ ጠላ) ይባላል፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ኢታርፍድ ሶስተኛዉ ደግሞ ጸላ ሐጼ ወይም (የአጤ ጠላ) ይባላል፡፡ ይህን ጸላ ሀጼ ንጉሱ በቃላቸዉ ካላዘዙ አይሰጡም፡፡

ከዚህ ዜና መዋእል የምንረዳዉ ከዚያ በፊት ያለዉን ባናዉቅም በሀገራችን በንጉስ ዘርዓ ያእቆብ ዘመን (1434-1468) ጠላ ይጠጣ እንደነበር ነዉ፡፡ ይህም ጠላ በትንሹ ከአምስት መቶ አመት በላይ ያስቆጠረ ድንቅ ባህላዊ መጠጣችን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ ትዉፊቱን ጠብቆ ከእኛ ዘመን የደረሰዉ መጠጥ ከስነቃሉ እንደተረዳነዉ ጠላ ተብሎ ስያሜዉን ያገኘዉ  ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በፊት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ የዘሬን አያድርገዉና በወቅቱ ጠላ እንደ ጠጅ በደረጃ የሚወርድ መሆኑም ከዜና መዋእሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ንጉሱም በስማቸዉ የተጠመቀ ጠላ እንዳላቸዉና ከእሳቸዉ ዉጭ ማንም እንደማይጠጣ እንካን ለሌላ ሰዉ ለራሳቸዉም ቢሆን ራሳቸዉ በቃላቸዉ ካላዘዙ እንደማይመጣላቸዉ ስናይ ጠላ ምን ያህል የተከበረ መጠጥ እንደነበር እንረዳለን፡፡













Thursday, June 22, 2017

የኢትዮጵያ ዜና መዋእል ጸሀፊዎች(Chroniclers) እና ገድል ጸሀፊዎች(Hagiographers ) እዉነት እንደሚጽፉ ማሳያ



በታሪክ ከምንጠቀማቸዉ ማስረጃዎች ዉስጥ የመጀመርያ ምንጮች ብለን ከምንመድባቸዉ ዉስጥ ዜና መዋእልና ገድላት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የመጀመርያ ደረጃ መረጃዎች እንደመሆናቸዉ ተአማኒነታቸዉና እዉነተኛነታቸዉም ላይ በጸሀፍያን ዘንድ ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጸሀፍት ዜና መዋእል ጸሀፊዎች(Chroniclers) እና ገድል ጸሀፊዎች(Hagiographers ) አንዳንዴ አጋነዉ ወይም አቅለዉ የራሳቸዉን ሀሳብ ጨምረዉ ተሪክ ይጽፋሉ ብለዉ ይሞግታሉ፡፡ የሁለቱ ሀሳቦች ሙግት እንዳለ ሆኖ ዜና መዋእል ጸሀፍያንና ገድል ጸሀፍያን በነበሩበት ጊዜ ለሚጽፉት ታሪክ እዉነታነት ምን ያህልጠንቃቃና ተአማኒ እንደሆኑ ተለያዩ ድርሳናቶቻቸዉ ያሳያሉ፡፡ 

ለማሳያ ያህል ለዛሬ ከዜና መዋእል ደራሲዉ ንጉስ ተብሎ የሚታወቀዉን የአጼ ዘርዓ ያእቆብን (1426-1460 ዓ.ም ) እና የልጁን የንጉስ በእደ ማርያምን Chronicler ስራ ከገድል ደግሞ የገድለ እስጢፋኖስን Hagiographers  ስራ እንይ፡፡ ዜና መዋእሉ እንደ አብዛኛዉ ገድላትና ዜና መዋእሎች ሁሉ በመጀመርያ የተጻፈዉ በግእዝ ሲሆን በ2007 ዓ.ም የልጁን የአጼ በእደ ማርያም ዜና መዋእል ጨምሮ በአለሙ ሀይሌ አማካኝነት ወደ አማርኛ ተተርጉሙዋል፡፡ የዜና መዋእሉ ጸሀፊ ሲጀምር በስመ እግዚአብሄር መጀመሩ የሚጽፈዉ የንጉሱ ዉሎ የግል አድሎ እንደማይኖርበት አመላካች ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወደዉስጡ ስንገባ ለተአማኒነቱና ከግል አስተያየቱ ነጻ መሆኑን የሚያስረዳን ድርሰቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በዜና መዋእሉ ገጽ 5 ላይ የምናገኘዉ ሀይለ ቃል ለዚህ እዉነታ ዋና ማስረጃ ነዉ፡፡  
ከዚህ በሁዋላ የሚገባዉን የሞት ቅጣት በርሱ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዘዙ፡፡ በእነርሱም ፍርድ ጉድጉዋድ ቆፍረዉ እርሱን ወደዚያ ጉድጉዋድ ጣሉት፡፡ ጻሰርጉዋ አምሃ ኢየሱስን እነሱ ያመነዘሩባትንም ያችንም ሴት ጭምር ወደ ጉድጉድጉዋዱ ወረወሩዋቸዉ፡፡ ከነርሱ ጋር በመተባበር የሰይጣን ከበሮ ብለዉ የሰየሙትንና ደብረ በኩር በተባለ ገዳም የመነኮሰዉን የደብረ ዳሞዉን ንቡረ እድ ኖብንም አብረዉ ወደ ጉድጉዋድ ጣሉት፡፡ ከዚያም አምደ ሰይጣንን ወደ አማራ አገር አጋዙት፡፡ ከንጉሱ በቀር ቦታዉን ለይቶ ማንም አያዉቅም፡፡ አምሃ ኢየሱስንና ሰይጣን ከበሮ የተባለዉን ኖብን ጎሽአሮ ወደተባለ ቦታ አጋዙዋቸዉ፡፡ ከአምደ ሰይጣን በፊት ቢትወደድ የነበረዉን ኢሳያስን ንጉሳችን ቀስት በምትባል ስፍራ በአማራ አገር ሳለ እንደ አጋዙት በጆሮየ ሰምቻለሁ፡፡ ማየት ግን ራሴ አላየሁም፣ሲይይዙትም አልነበርኩም፡፡ በዚያም በፈጸመዉ በደል ምክንያት የብረት ሰንሰለት በአንገቱአጥልቀዉ አጋዙት የተጋዘበትንም ቦታ ግን አላወቅሁትም፡፡
እንግዲህ ዜና መዋእል ጸሀፊዉ የሰማዉን ነገር ዝም ብሎ እንደሰማ መጻፍ ሲችል በጆሮየ ሰምቻለሁ ማየት ግን ራሴ አላሁም ብሎ እንዲጽፍ ለምን ተገደደ፡፡ ዝቅ ብሎስ በበደሉ ምክንያት እንደተጋዘ እርግጠኛ ሆኖ ሳለ እንዴት የተጋዘበትን ቦታ ግን አላዉቅም ብሎ እንዲጽፍ ተገደደ፡፡ ይህ ሁሉ የጸሀፊዉ ጭንቀት የሚያስረዳን እዉነታን ለመጻፍ ካለዉ ጥንቃቄና ተአማኒነት የመነጨ ነዉ፡፡
በአጼ በእደማርያም ዜና መዋእል ገጽ 50 ላይ ጸሀፊዉ ከራ ፈጠራ የነጻ እዉነትን ብቻ የሚጽፍ መሆኑን እንረዳበታለን፡፡ንጉሱ ወደ አዳል በሄደ ጊ ያገኛቸዉን ሾሞች ጸሀፊዉ ሲዘረዝር እንዲህ አስቀምጦዋቸዋል፡፡
…….. የእነዚህም የሹመት ስም ጎሳች ጌታሲድ፣ አህመድ፣ እስር ገራድ፣ ግደይ ገራድ፣ ኮሽም ገራድ፣ ሀርጋይ ገራድ፣ ፈራሽ ሹም ይባላሉ፡፡ እነዚህ ስማቸዉን የማዉቃቸዉ ናቸዉ፡፡ ስማቸዉን ያላወኳቸዉ ሌሎች ብዙ የአደል ሹሞች ነበሩ፡፡
በገጽ 56 ላይ ንጉሱ የአትሮነሰ ማርያምን የክብር ስነ ስርአት መፈጸሙን ካህናቱንና ሰራዊቱን መሸለሙን አትቶ ባለቤቱን ስለማንገሱ እንዲህ ይጽፋል፡፡
……በዚያም ግራ በዓልቲሀት ንግስት ዠን ሴፋን እንደወጉና እንደህጉ በዚች እለት አነገሱዋት፡፡  ስርአተ ንግሱን በአይኔ አላየሁም፡፡ በዚያ ቁሜ ሳለሁ ሚስጥራዊ የሆነዉን ህጋቸዉን እንዳላይ በፊቴ የሀር መጋረጃ ጋርደዉብኝ ነበር፡፡
ከዚህ የዜና መዋእል ክፍል ጸሀፊዉ እዉነት እንደሚጽፍ ማሳያዉ ንጉሱ ሚስጢር እንዳያይ መከልከሉን እንኳ ይፈርድብኛል ብሎ ሳይፈራ ያላየዉን ነገር አላየዉም ብሎ መጻፉ ነዉ፡፡ በገጽ 68 ሌላኛዉ እዉነተኛ የአይን ምስክርነት ማሳያ ደግሞ እንደሚከተለዉ ይነበባል፡፡
ንጉሳችን እርሱ ግን ከዚያች ምድር ተነስቶ ምድረ አራራ ወደሚባለዉ ሀገር ሄደ፡፡ በዚያች ሀገር ለጥቂት ጊዜ ተቀመጠ፡፡ የበአለ ጥምቀትንም በአል በዚያ አሳለፈ፡፡ በዚህም ወቅት ከነገሰ ሰባት አመት ሞልቶት ነበር፡፡ ከዚህ በሁዋላ የተደረገዉንና የተሰራዉን ስራ ሁሉ ግኔ እኔ ላዉቅና ልገነዘብ አልቻልኩም፡፡ ከህጻናቱ ጋር እኖር ዘንድ ልኮኛልና፡፡
የአቡን እስጢፋኖስ ገድል ጸሀፊን ተአማኒነት ያስረዳልኛል ብየ ለማሳያ የመረጥከትን ወደ ማሳት እገባለዉ፡፡ አቡነ እስጢፋኖስ በአጼ ይስሀቅ እና አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሰት እስጢፋኖስ በይስሀቅ ዘመነ መንግስት በ15ኛዉ መክዘ የነበሩ ናቸዉ፡፡ በጊዜዉ ከሁለቱም ነገስታት ታላቅ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ በጊዜዉ በግዕዝ  የተጻፈዉን ይህን ገድላቸዉን ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ በ1996 ዓ.ም ወደ አማርኛ ተርጉመዉታል፡፡ በመጽሀፉ በገጽ 119 ላይ ደራሲዉ ገድሉን ሲጽፍ የራሱን ሀሳብ ላለማስገባት እና እዉነተኛ ገድል ለመጻፉ ማስረጃ እናገኛልን፡፡ ሙሉ ንባቡን እንይ፡፡
የቅዱሳን ገድላቸዉንና ሰማእትነታቸዉን በመጽሀፍ ለሰዉ ማሳየት ለእኔና ከእኔ በሁዋላ ለሚመጡ እንደኔ ላሉት ጠቃሚ እንደሆነ ሀሳብ ሲመጣብኝ ከብዙ ቀናትና አመታት በሁዋላ ከእኔ በፊት የሆነዉን እየጠየቅሁ በእኔ ጊዜ የሆነዉን እንዳማዉቀዉ አደርገዉ ዘንድ ወደድኩ፡፡ ግን ከሀገሩ ርቀት የተነሳ ከማህበሩ አለቃ ፈቃድ አላገኘሁም ነበር፡፡ ተፈቅዶልኝ ቢሆን ኖሮ በየጊዜዉ የሆነዉን ወድያዉ በዝርዝር እጽፈዉ ነበር፡፡ባለመሆኑ ስራዉ አንሱዋል፡፡ ታሪኩም አጭር ሆኑዋል፡፡የመንፈስ አባታችን ሊቀ ማህበሩ ሲፈቅድ ከወንድሞች አንዱን ይዤ ከሚያዉቁ ዘንድ እየሆንንም በእነዝያ ዘመናት የሆነዉን ሁሉ ተነጋገርንበት፡፡