http://twondifraw.blogspot.com/

Wednesday, December 6, 2017

የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ

በህብረተሰቡ ዘንድ በእለት ተእለት ኑሯችን በንግግሮቻችንም በጽሁፎቻችንም የምንጠቀማቸዉ ብዙ ሀገር በቀል አባባሎች አሉን፡፡ እኒህ አባባሎች ሰፊዉን ጠበብ፣ ከባዱን ቀለል፣ ደረቁን ረጠብ አድርገዉ መልእክትን በማቀላጠፍ እኛንም በማግባባት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸዉ፡፡ የእኒህ አባባሎች ዛሬ ላይ ባለቤታቸዉ ህዝብ እና ህዝብ ብቻ ነዉ፡፡ እኔ ግን ፍለጋየ እና ቢሆንልኝ የምደሰተዉ እኒህን አባባሎች ለመጀመርያ ጊዜ ከአፉ አዉጥቶ የተናገራቸዉ ግለሰብ ማን እንደሆን ማወቅ ነዉ፡፡ መቼም ህዝብ በአንድ ቅጽበት አይናገራቸዉም፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንመለከት ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም ያለዉ የመጀመርያዉ ግለሰብ ማን ይሆን? እግር አልባ ሰዉ ይሆን፣ ዛፍ ቆራጭ ይሆን፣ ነጋዴ፣ ገበሬ፣ ሙህር፣ ቄስ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ከየትኛዉ ወገን ይሆን፡፡ እነ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ፣ እነ ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል፣ እነ አህያዉን ቢፈሩ ዳዉላዉን፣ እነ አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣ እነ አንድ ሞኝ የተከለዉን ሰላሳ ሊቃዉንት አይነቅለዉም አረ ስንቱ፡፡ ማን ይሆን አስቀድሞ በሆዱ አጭቶ ከአፉ ያወጣቸዉ፡፡
እኒህ ሰዎች ሊደነቁ ሊወደሱ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነሱ የተናገሩት የመላዉ ህዝብ ሀብት ሆነ፣ እኛም በንግግሮቻችን ጣልቃ እያስገባን የተንዛዛ ሀሳብ አሳጥረናል፣ ሊቅነታችንን አስመስክረንበታል ወ ዘ ተ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ራሳችን የፈጠርናቸዉ መስሎናል፡፡ አንድ አስገኝ ግለሰብ እንዳላቸዉ አስበንም አናዉቅም፡፡ እርግጥ ነዉ በማህበረሰቡ የሚነገሩ አንዳንድ አባባሎች ለመጀመርያ ጊዜ የተናገራቸዉን ግለሰብ የሚጠቁሙ ጥቂቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በአንድ ህብረተሰብ ዘንድ የሚነገሩትን ባነሳ ጣጣ ነዉ አለ ቆምጨ አምባዉ፣ ምን ታደርጊዋለሽ አለ ጥላዉን ገሰሰ፣ ተጨንቄብሽ አለ አለሙ ብርሀኔ፣ ልግብ አለ ዳምጤ ብርሀኑ፡፡ ሁሉም አስገኛቸዉን ይናገራሉ፡፡  ይህ ማህበረሰብ የሰለጠነ ነዉ ባይ ነኝ፡፡ ለምን ቢሉ በንግግራቸዉ ወቅት ምንም እንኳ አባባሎችን ቢያስቀድሙም ተናጋሪያቸዉን ያስከትላሉና፡፡ ከፕላጃሪዝም (ከባባቤትነት ስርቆት) የጸዱ ናቸዉ፡፡ ብዙዎች አባባሎቻን ግን በሀይለኛዉ ፐላጃራይዝድ የተደረጉ ናቸዉ፡፡ ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሱት እነ በአንድ ድንሃይ ሁለት ወፍ፣ እነ ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል፣ እነ አህያዉን ቢፈሩ ዳዉላዉን፣ እነ አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣ እነ አንድ ሞኝ የተከለዉን ሰላሳ ሊቃዉንት አይነቅለዉም ሁሉም ምንም እንኳ አንድ አስገኝ ግለሰብ ቢኖራቸዉም ህዝቡ ሲናገራቸዉ ግን የራሱ አስመስሎ ነዉና የባለቤትነት ስርቆት ተጎጅዎች ናቸዉ፡፡
እኔም በንግግሬ ወቅት ዘመናዊ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ የሙህራንን የመመረቅያ ጽሁፍ የሚያስተችና የሚያጎድፍ ፕላጃሪዝም የተባለ ወንጀል ሁል ጊዜ በምላሴ ስፈጽም እየሰቀጠጠኝ ነዉና፡፡ ይህ የአባባሎቻችንን ባለቤት ማወቅ ጉጉቴ የመነጨዉ በዋናነት ካለእነሱ ንግግር ስለማይሆንልኝ ከፕላጃሪዝም ለመንጻት ነዉ፡፡ የምመኘዉም እድሌ ሰምሮ እንደ እናቶቼና አባቶቼ እየተገረምኩ በወሬዎቼ መካከል ሆሆ ….. አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል አሉ አቶ እገሌ፣ እም እቴ……. ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል አሉ እሞሀይ ማንቴስ……… እያሉ ከፕላጃሪዝም የጠራ ዘመናዊ ንግግር ማድረግ ነበረ፡፡
እናም ይህ የአባባሎቻችንን የመጀመርያ ተናጋሪ ሰዉ ማንነት በትክክል የማወቅ ፍላጎቴ እንደማይሳካ ስረዳ ለመገመት ተገደድኩ፡፡ ለአሁኑ ልገምት የተነሳሳሁበት ከአባባሎቻችን መካከል የሆነዉን “የአንድ ሳንቲም ሁልት ገጽታ” የሚለዉን ነዉ፡፡ ይህን አባባል ተናግሮ ያናገረን ሰዉ ምን አይነት ይሆን? የሚለዉን ጥያቄ በግምታዊ መላምት ከመለስኩ በሁዋላ እምልላችኋለሁ አባባሉን እንደ ድሮዉ እንደወረደ አልናገረዉም፡፡ ይልቁንም የአስገኝዉን ስም እየጠቀስኩ አለ እገሌ እያልኩ ባለቤቱን እያወጅኩ ከፕላጃሪዝም ነጻ ሆኜ አወራለሁ እንጅ፡፡ ለማንኛዉም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ባይን ግለሰብም ይሁን ድርጅት ማንነት ፍለጋ ገባሁ፡፡
አንድ ሞኝ የተከለዉን ሰላሳ ሊቃዉንት አይነቅሉትም ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ችግሩ ፕላጃሪዝም ነዉ እንጅ  እኔም ለራሴ አልፎ አልፎ ተጠቅሜዋለሁ፡፡ እዉነቱ ይሄ ሁኖ እንጅ  የአንድን ነገር ፍጹም አንድነትና አይነጣጠሌነት ለመግለጽ ብሎም ለማስረዳት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ብሎ ለመጀመርያ ጊዜ የተናገረ ሰዉ ከሞላ ቁሳቁስ ሳንቲምን ብቻ ለመጠቀም የተገደደዉ መለኮታዊ ትእዛዝ አልያም ሌላ የተለየ አሳማኝ ምክንያት አግኝቶ አይመስለኝም፡፡ አሁን ባለንበት ቅጽበት ዞር ዞር ብለን ብናይ እኮ በዙርያችን የማይነጣጠሉ ግን ሁለት ገጽታ ያሉዋቸዉ ስንት ግሳንግስ ነገሮች አሉ መሰላችሁ፡፡ እስኪ ከራሳችሁ ጀምራችሁ የቤት እቃዎቻችሁን እዩ፡፡ እኔ አሁን አልጋየ ላይ ጋደም ብየ ይህን ስጽፍ ከፊት ለፊቴ ሶስት ተደራርበዉ የቆሙ የእናቴ የእንጀራ ማቅረብያ ትሪዎች ይታዩኛል፡፡ ሶስቱም ሁለት የማይነጣጠሉ ገጽታዎች አሉዋቸዉ፡፡ ፊትና ጀርባ፡፡ እንዳዉም እንደሳንቲም ሁሉ ዘዉድ የለዉም እንጅ ጎፈር አለዉ፡፡ የጃንሆይን ባንዲራ በቀጭን ዘንግ ሰክቶ በትክሻዉ ያነገተ ጎፈርያም አንበሳ ከፊት ከፊታቸዉ ላይ ተነድፎበት ይታያሉ፡፡ ዙርያዉን ነዉ ያልኩትና የማይነጣጠሉ ገጽታዎች ፍለጋ ወደ ጀርባ ዞሬ ሳይ ብፌ ላይ የቤተሰብ የፎቶ ፍሬሞች ከነፎቶዎቻቸዉ ተኮልኩለዉ ይታዩኛል፡፡ እነሱም ያዉ ናቸዉ፡፡ የምን ሩቅ መሄድ አስፈለገ የለበስኩት ብርድ ልብስ ለራሱ ጥሩ ምሳሌ አይደል እንዴ፡፡ የማይነጣጠል ሁለት ገጽታ አለዉ፡፡ እንዲህ ዘና የምልበት ቤቴ ራሱ ጣርያዉ፣ ኮርኔሱ ግድግዳዉ በሩና መስኮቱ የሚገርም ባለ 2D ናቸዉ፡፡
ሰዉ ግን ሳንቲምን ዝም ብሎ ዘሎ የተጠቀመ አይመስለኝም፡፡ እንዳዉም ለምን የሚል ጥያቄ አንስቶ ጥልቅ ጥናት የሚያስፈልገዉ ይመስለኛል፡፡ እንደኔ ግምት ግን ለዚህ ሰዉ ከሌሎች ገጽታዎች ሁሉ ልቆ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ትልቅ ዋጋ ሳይኖራቸዉ አልቀረም፡፡ ለማንኛዉም ግምታዊዉን ምላሽ ለማግኘት ይረዳን ዘንድ ሳንቲሞች በአብዛኛዉ ወደሚገኙበት ሰፈር ጎራ ማለት ግድ ይለናል፡፡ ሳንቲሞች ከሚዘወተሩባቸዉ ቦታዎች መካከል ገበያ አንዱና ዋነኛዉ ስፍራ ነዉ፡፡ ነገር ግን ገበያ ላይ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ምንም ዋጋ የላቸዉም፡፡ ለገጽታቸዉ ማንም ዋጋ አይሰጣቸዉም፡፡ ስለዚህ ገብያተኛ ይህን አባባል አልተናገረዉም ብለን መላምት መንደፍ እንችላለን፡፡ ሁለተኛዉ የሳንቲም መገኛ አድራሻዎች ደግሞ ቁማር ቤቶች ናቸዉ፡፡ ከራሴ ልምድ ተነስቼ ከገበያ ይልቅ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ትልቅ ዋጋ ያላቸዉ በቁማር ቤት ብቻና ብቻ መሆኑን ማሳየት እችላለሁ፡፡

የአንድ ሳንቲም ሁለቱ ገጽታዎች የተለያዩ ስሞች መኖራቸዉን የምናዉቀዉም አሁንም በቁማር ጊዜ ብቻ ነዉ፡፡ አንድ ቀን አንዱም ገጽ አቤት ብሎ አያዉቅም እንጅ ቁማርተኛ ሁሉ እኒህን ገጽታዎች ስማቸዉን እያቆላመጠ ሲጠራቸዉ ነዉ የሚኖረዉ፡፡ አንዱን ገጽ ጎፋ (ጎፈር) እያለ ይጠራዋል ሌላኛዉን ዘዉድ ይለዋል፡፡ ታድያ በመቆመር ጊዜ እኒህን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ስሞች ግብሮችና ልዩ ምልክቶች ጠንቅቆ ማወቅ አዉቆም በገጽ መጥራ ተቀዳሚ መስፈርት ነዉ፡፡ ይህ እዉቀት የራስን ገንዘብ ፈቅዶ ተጫዉቶ ከመበላት አልያም ካሸነፉ የቋመጡለትን የአቻን ገንዘብ እንዳያመልጥ ሞልቅቆ ለማምጣት ቁልፎች ናቸዉና፡፡ የጨዋታዉ ሰልፍ ይህን ይመስላል፡፡ ሲቆመር ሳንቲም  የያዙ የቆማሪ መዳፎች አንዱ ባንዱ ላይ ተደራርበዉ የገበሎ አስተኔ ስብስብ መስለዉ ይቀመጣሉ፡፡ ከእያንዳንዱ መዳፍ እቅፍ ዉስጥ ላብ የሚያጠምቃት በዘዉዱ ይድፋት በጎፈሩ ባለቤቱ ብቻ የሚያዉቃት ሳንቲም ትወሸቃለች፡፡ ከዚያም በላይ ያለዉ ግለሰብ መዳፉን ያነሳና ሳንቲሙ የወደቀችበትን የላይኛዋን ገጽ በጥንቃቄ ያያል፡፡ ቀጥሎ ከስር ያለዉ ተጫዋች መዳፉን ቀስ ብሎ ያነሳና እንዲሁ የሳንቲሙን የላይኛዉን ገጽታ ያሰተዉላል፡፡ የእሱ የሳንቲም ገጽታ ከላይ ከነበረዉ የሳንቲም ገጽታ ጋር ከተመሳሰለ የላይኛዉ ገንዘቡን ይወስዳል (በእነሱ አባባል ይበላል) የታችኛዉ ተጫዋች ሳንቲም ገጽታ ከላይ ካለዉ ከተለየ የታችኛዉ ይበላል፡፡
አዎ ለመበላላትም ላለመበላላትም ቁማርተኞች የአንድን ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች የራሳቸዉን ያህል ያዉቁዋቸዋል፡፡ በቁማርተኞች ዘንድ የአንድን ሳንቲም ሁለት ገጽታ ማወቅ ከመበላት ያድናል፡፡ እኛ ከመበላት የምንድነዉ መሳርያ ታጥቀን ዋሻ ገብተን ቤት ዉስጥ ዘግተን አይደለ፡፡ ስለዚህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ለቁማርተኛ የመሳርያ የቤትና ዋሻ ያህል ናቸዉ ማለት ነዉ፡፡ ይህ እንግዲህ አንድ ሀቅ ያሳየናል፡፡ እሱም የአንድ ሳንቲም ሁለትጽታ ብሎ የተረተዉ፣ የተናገረዉ የመጀመርያዉ ግለሰብ የሳንቲም ገጽታዎች ህይወቱ የሆነዉ ቁማርተኛ ሰዉ መሆኑን ነዉ፡፡ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ዋጋ ያላቸዉ ለቁማርተኛ ብቻ ነዋ፡፡ ለነጋዴዉም ሆነ ለገበሬዉ ለለማኙም ሆነ ለሙህሩ ዋጋዉ ራሱ ሳንቲሙ እንጅ የሳንቲሙ ገጽታዎች አይደሉም፡፡ አስተዉላችሁ ከሆነ በንግድ ጊዜ ሰዎች ሳንቲም ሲቀያየሩ የሚመለከቱት አምስትነቱን፣ አስርነቱን፣ ስሙኒነቱን፣ ሽልንግነቱን ዛሬ ዛሬ ደግሞ አንድ ብርነቱን እንጅ እንደቁማርተኞች ዘዉዱንና ጎፈሩን ወይም ገጽታዉን አይደለም፡፡ በቁማር ጊዜ ደግሞ  ዘዉዱነት ጎፈርነት እንጅ ስሙኒ ሽልንግነት ከቁብ አይገቡም፡፡ ለዚህም አይደል እንዴ ባለዘለሰኛዉ በቁማርተኞች የሳንቲሞች ዋጋ ሳይሆን ገጽታ መለከፍ ተደንቆ የተቀኘባቸዉ እንዲህ ሲል
ቁማር ጨዋታ ተጫዉቼ፣
አጨብጭቤ ቀረዉ ተረትቼ፣
ምንኛ እድሌ በሰመረ፣
ዘዉዱን ገልብጨ በነበረ፡፡
የቁማርተኛ ጥቅስ እንዲህ ይጠቅማልና አንድነትን ለማወፈር ተመሳሳይነትን ለማጠንከር አንድ ቁማርተኛ የተከለዉን  እኛም ሰላሳና ከዚያ በላይ ሆነን ይህን ቃል ሳንነቅለዉ ስናስተጋባዉ እንኖራለን፡፡ ታድያ ከዚህ ወድያ ከባለቤትነት ስርቆት ተላቅቄ የሰለጠነ ንግግር ልናገር ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ አለ ቁማርተኛ እያልኩ፡፡











Monday, July 3, 2017



ነገረ-ጠጅ
(የተጣለ መጠጥ)
እነሆ በሀገራችን መጠጥ ይጣላል (ጠጅ) ይሾማል (ጠጅ) ይበጠበጣል (ጠላ) ይጠመቃል (ጠላ) ይወጣል (አረቂ)፡፡ እኒህን ሀገር በቀል አባት አደር ባህላዊ መጠጦች አንድ የሚያደርጋቸዉ ባህርይ አላቸዉ፡፡ የእኛን ሙሉዉን ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ዘመን አያድርገዉና መጠጦቹ የሚጣልባቸዉ፣ የሚሾምባቸዉ፣ የሚበጠበጥባቸዉ፣ የሚጠመቅባቸዉና የሚወጣባቸዉ እቃዎች ከሸክላ መሰራታቸዉ ነበር፡፡ በኋለኛዉ በእኛ ዘመንማ ቫይረስ ይከላከል ይመስል የላስቲክ እቃ ሁሉ ሸክላን እየገፈተረ ጥልቅ ማለት ጀመረ፡፡ እኒንያ የሸክላ እቃዎች ማሰሮ፣ እንስራ እና ጋን ናቸዉ፡፡ ጋን ከሸክላ የሚሰራ የወግ እቃ ሲሆን ምናልባትም በሀገራችን ከባህላዊ የቤት ቁሳቁሶች ትልቁ ሳይሆን አይቀርም፡፡በሃገራችን በነገስታት ዘመን አንድ ታላቅ ጋን እጅግ ማለፍያ የሆነ አገልግሎት ነበረዉ፡፡ እርሱም ለንጉሱና ሹማምንቶቹ የሚሆን ባለሙያ ሴት የጠመቀችዉ ጠጅ መሾምያነት ማገልገል ነበር፡፡ ጠጅ እጅግ የተወደደ የክብር መለክያ የሆነ መጠጥ ስለነበር በከበረ እቃ ማለትም በጋን ተሹሞ ጋኑም በክብር ቦታ ለብቻዉ በእልፍኝ ዉስጥ ይቀመጣል፡፡ ጠጁ በጋን መዘጋጀቱ ከጠጁም ከጋኑም ክብር የተነሳ ጠጁ ጋን ተሾመ እሰከመባል ድረስ የሹመት ማእረግ ነበረዉ፡፡ ይህ በጋን የተሾመዉ ጠጅ በንግስናና በምስፍና ለተሸሙት ሰዎች በማእረግ ይወርዳል ይጠጣል፡፡  

ዉሎ ዉሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከሞት አይቀርምና ሹመት ይሻራል ንግስናም ይቀራል፡፡ በሀገራችን ንግስና ሲቀር ጠጅም መሾሙ ቀረ፡፡ መጠጣቱ ግን አልቀረም፡፡ ንግስና ከቀረ በኋላ ኢትዮጵያዊት እናት ጠጅ ሾምኩ ሳይሆን የምትለዉ ጠጅ ጣልኩ ነዉ፡፡ እናም አባቶች  የነገስታትን ዘር ተዋግተዉ አዳክመዉ ንጉስ በዙፋን መሾም ሲቀር እናቶች ደግሞ ጠጅ በጋን መሾሙን አቁመዉ በሮቶ መጣል ጀመሩ፡፡ እናቶች ጠጅ ጣልኩ ይበሉን እንጅ እንዴት እንደጣሉት ያወቁ አይመስለኝም፡፡ጊዜ ሰጥቷቸዉ እስከዚህ ዘመን የደረሱ የተሾመም የተጣለም ጠጅ የጠጡ አዛዉንት አባቶች እንደሚናገሩት ከሆነ እናቶች ጠጅ መጣል የጀመሩት በሶስት መንገድ ነዉ ይላሉ፡፡

  • ·         ማር ለከለር ብቻ ተጨምሮ ጠጁ በስኳር መጠመቅ ሲጀምር፡
  • ·         ጋን ከእልፍኝ ጠፍቶ ማድቤት በተቀመጠ ጎማ ሲጠመቅ፡፡
  • ·         ለንጉስ ቀርቶ ለህዝብ መዉረድ ሲጀምር ጠጅ መጣሉ ተጀመረ፡፡

ታድያ እኒህ አባቶች ስናገሩ እንደምንሰማዉ ከሆ በሀገራችን የጠጅ ሹመት ከንግስና ሸረት ጋር አብሮ ከስሞ ቀርቷል፡፡

ከላይ አብረን እንዳየነዉ የተሸመ ጠጅ ደንበኞች የማንም አልፈ ሂየጅ ሳይሆን ነገስታቱ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱና ልኡላኑ ነበሩ፡፡ የተጣለ ጠጅ ደንበኞችሳ አትሉኝም፡፡ እነሱማ  አብዛኛዎቹ ኑሮ የጣላቸዉ የሚመስሉ ሊጠጡ ሲሄዱ ትያትር ሲተዉኑ ቆይተዉ ከመድረክ ወረዱ የሚመስሉ ናቸዉ፡፡ እንዴት ቢሆን አትሉኝም፡፡ እንዲህ ነዋ፡፡ አለባበሳቸዉንስናይ ከመሃል በእላቂ ካፖርት አልያም ረጅም ጃኬት ዉስጥ የተደበቁ ከታች ባት ከጉልበት በሚሸፍን ቦት ጫማ ገብተዉ የሚንደፋደፉ ከላይ ደግሞ አይንና አፍንጫን አፍና የምትይዝ አሮጊት ኮፍያ ያጠለቁ በእድሜ አባዋራ፣ ወጣትዋራ እና አሁን አሁን ደግሞ እማዋራ የሆኑ ናቸዉ፡፡ እኒህ ዋራዎች አካሄዳቸዉን ስናይ የተጣለዉን ጠጅ ለመጠጣት በእጃቸዉ ሰንጣራ ዘንግ ወይም ከዘራ ተመርኩዘዉ ሰአት አመራረጣቸዉ ደግሞ ጸሀይ ብቅ ወይም ዘቅዘቅ ስትል ማዝገም የሚጀምሩ ናቸዉ፡፡ የሚገርመዉ የአሁኑ ጊዜ ጠጅ መጣሉ ብቻ ሳይሆን መጣሉ (አላልተህ አንብብ) ጭምር ነዉ፡፡ እናም እኒህ የጠጅ ደንበኛ ዋራዎች እንዲህ ከእግር እስከ ራሳቸዉ መልበሳቸዉ ጠጁ እንደሚጥላቸዉ ስላወቁ ነዉ ተብለዉ ይታማሉ፡፡ እንዳይወድቁ ዘንግ ወይም ከዘራ ይመረኮዛሉ፡፡ ዘንጉ አልችላቸዉ ብሎ ከወደቁ ወድቀዉ እንዳይቀሩ ቅልጥማቸዉን በቦት ወገባቸዉን በካፖርትና አናታቸዉን በኮፍያ ከጉዳት ይከላከላሉ፡፡ በተለይ የኮብልሰቶን መንገድ ከመጣ ወዲህ እንዲህ እንዲቀጥሉ አስገድዷቸዋል፡፡ አንድ በማህበረሰባዊ ህይወት ዙሪያ ዳሰሳ እያደረገ በብሎግ ለህብረተሰቡ መረጃ ሚያጋራ ጦማሪ እንዲህ ጦምሮ ነበር፡፡ መንግስት ህዝቡ እንዲወድቅ የቢራ ፋብሪካዎችን ይከፍታል፣ ወድቆ እንዳይነሳ ደግሞ ኮብልሰቶን መንገድ ይሰራል፡፡ የጠጅ ደንበኛ ዋራዎች ግን አልሞት ባይ ተጋዳይ ነቄዎች ስለሆኑ ወድቀዉ እንዳይቀሩ መንግስትን ይፎካከራሉ፡፡
 
በጃንሆይ ዘመን ከነበሩት ሀገር ወዳድ መኳንንት መካከል በላይ ዘለቀ የጎጃሙ ጀግና ይገኝበታል፡፡ በላይ ዘለቀ ጠጅ ያሾምበት የነበረዉ ትልቅ ጋን ነበረዉ፡፡ይህ ጋን አሁን በምስራቅ ጎጃም ዞን ልዩ ስሙ ሶማ ከተባለ በርሃማ ቦታ ይገኛል፡፡ ሶማ በርሃ በላይ ዘለቀ ጣልያንን ሲወጋ መሽጎ የነበረበትና በመጨረሻም በጃንሆይ ወታደሮች ተላልፎ የተሰጠችበትእጉም ብሎ የተጠለለባትን ሰዉ አሳልፋ ሰጠች የቦታ ባንዳ ነች፡፡ ታድያ አሁን የበላይ ጋን ጠጅ የሚሾምበት ቀርቶ ጠጅ የሚጥልበት ሰዉ እንኳን ስለጠፋ የዞኑ ቅርስ ሆኖ የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን ተገደደ፡፡ይህን አይነት ታሪክስናገኝ ደግሞ ወደፊት ጠጅ ከነመጣሉ እንኳ እንዳይቀር ያሰጋል፡፡የነጃንሆይ ጋን የት ደርሶ ይሆን፣ የአጼ ሚኒሊክስ ዕንጦጦ ማርያምን ሲያስመርቁ ከጋን ተርፎ ጠጅ ያሾሙበት ጉድጓድ ምን ሆኖ ይሆን?

ጠጅን ስናስብ በጣም የሚያሳዝነዉ ነገር በእጅ ጣት በማትቆጠር እድሜ ዉስጥ  ከንጉስ ተላልፎ ለህዝብ መናኘቱ ከእልፍኝ ወጥቶ በገበያ ላይ መዋተቱ ነዉ፡፡ ጠጅ ቸርቻሪዎችም መቸርቸርያዎችም እንደ “ቸርች” ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቡ መምጣት ይዘዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ ጠጅ ቤቶችና የጠጅ ደንበኞች በየሰፈሩ በየጉራንጉሩ የበዙት ለምንድን ነዉ? የሚል፡፡ እኔ ግን ጠጅ መሾሙ ቀርቶ መጣል ስለጀመረ ነዉ እላለሁ፡፡ የሚያሳስበዉ ነገር ግን ጠጅ መጣሉ አይደለም መሾሙ እንደቀረ መጣሉ ሲቆም ጠጅ ምን እንደሚሆን ነዉ፡፡
አዎ በነገስታ ዘመን ጠጅ አይጣልም ነበር፡፡ ይሾማል እንጅ፡፡ ለተራ ሰዉም አይሰጥም፡፡  የሚገርመዉ ጠጅ በተራ ሰዉ አለመጠጣቱ ሳይሆን በእንዲህ አይነት ሰዎች ቤት እንኳን አይሾምም ነበር፡፡ የሾመ ሰዉ ቢገኝ ቅጣት ነበረዉ፡፡ ጠጅ ለመሾም አንድ ሰዉ ማእረግ ያለዉ መሆን ነበረበት፡፡ አይ ጠጅ የነበረዉ ክብር ኖሯል አያ፡፡ እስኪ ይህን ታሪክ በማስረጃ እንይ፡፡ 

“………… See how our learnd and pious people lower themselves to an earthly king?” Berhan whispered into my ear. “one other thing Tewaney, Teji flows like water here but you and I can’t brew it at home, even if we wanted to, unless such a title such as Landowners or Kegnazmach or have fought in the flanks of a prince, or killed or captured enemy. People brew it secretly, though. If they are caught it will be confiscated and they may even face flogging, I find this truly detestable” (source Hiwot Teffera, Mine to Win 2016 p.138)
በግርድፉ ሲተረጎም 
…………..ብርሀን በጆሮየ እንዲህ ሲል አንሾካሾከ፡፡ ተመልከት የእኛ ህዝብ ራሱን ለምድራዊዉ ንጉስ እንዴት እንደሚያጎበድድ፡፡ ሌላኛዉ ተጨማሪ ነገር ተዋናይ፣ እዚህ ጠጅ እንደዉሃ ይፈሳል፣ እኔና አንተ ግን በቤታችን መሾም አንችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ማእረግ ማለትም ቀኝ አዘማችነት፣ የመሬት ባላባትነት ከሌለን አልያም ከንጉስ ወታደር ጎን ተሰልፈን ጠላት ካልማረክን ወይም ካልገደልን ጠጅ መሾም ብንፈልግም አንችልም፡፡ ሰዎች ተደብቀዉ ጠጅ ይሾማሉ፡፡ ከተያዙ ግን ጠጁን ይቀማሉ እንዳዉም በጅራፍ ይገረፋሉ፡፡ በእዉነት ለመናገር ይህ ለእኔ አስከፊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ከ Mine to Win መጽሀፍ እንደምንረዳዉ ተዋናይ የቆሎ ተማሪ ሲሆን በ1857 የእድ ዉሃ አካባቢ ተወልዶ  በ1870ዎቹ በደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም ፊደል፣ ንባብ እና ዜማ ተምሯል፡፡ ቀጥሎ ዋሸራ ማርያም በመሄድ ቅኔ ከሊቀ ሊቃዉንት ብርሀነ ሰረገላ ታየ እግር ስር እየተማረ በነበረበት ወቅት ቀኝአዝማች ሳህለማርያም የሚባል አንድ የመሬት ባላባት ድግስ ጠርቷቸዉ ጠጅ እንደ ዉሃ ሲጠጣ አስተዉሏል፡፡ በዚህ ወቅት አስተማሪዉ ሊቀ ሊቃዉንት ብርሀነ ስለጠጅ ምንነት በወቅቱ ምን እንደሚመስል ቅኔ በለመደዉ አፋቸዉ አሳምረዉ ለተማሪያቸዉ ተዋነይ ያስጨበጡት ቁም ነገር ለእኔም ጠጅ ዛሬ እንደተጣለ ያኔ እንዴት እንደተሾመ መጣጥፌ ትልቅ ማስረጃ ሆኖልኛል፡፡